
አባታችን ይህን ቃለ ውግዘት ካስተላለፉበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከምእመናንና ከተለያዩ ክፍሎች ውግዘቱን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች በቃልና በጽሑፍ፥፣ እንዲሁም በተለያዩ ጋዜጦች ላይ የቀረቡላቸው ሲሆን፤ ለቀረቡት ጥያቄዎችም ተገቢ የሆኑ ምላሾችን ሰጥተዋል ሰጥተዋል። በተለያዩ ጊዜዎች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል በ፲፱፻፺ ዓ/ም ብዙ ምእመናን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው በጋራ ያቀረቡላቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ "በዚህ ውግዘት መካከል በእርስዎ ወይም በሳቸው መካከል የመለየት ባሕርይ ቢኖር ውግዘቱ እንደ ታሰረ ነው ወይስ እንደ ተፈታ ነው የሚቆየው? ውግዘቱን ማን ይፈታዋል? እስከ መቼ ድረስ ነው ውግዘቱ የሚቆየው?" የሚል ሲሆን፤ ክቡር አባታችን የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተው ነበር።

በወቅቱ የቀረቡት ጥያቄዎች በርካታ ሲሆኑ፤ እንደ አግባቡ መልስ ተሰጥቶባቸዋል። እኛም እነዚህ ጥየቄዎችና መልሶች አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ሁኔታ የሚያመላክቱና መፍትሔ የሚጠቁሙ ሆነው ስላገኛናቸው ለእናንተ ለምእመናን ለማቅረብ ወደድን። በ፲፱፻፺ ዓ/ም ምእመናን በሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌ ታምሩ መኖሪያ ቤት ተገኝተው በወቅቱ ያቀረቡላቸው ፳ ጥያቄዎች፦
፩፦ ውግዘት ማለት ምን ማለት ነው?
፪፦ አንድ ሠው ተወገዘ ሲባል ምን ምን ሲሰራ ነው?
፫፦ በፓትርያሪኩና በእርስ መካከል የተፈጠረው ችግር ለመፍታት ለምን አልተቻለም?
፬፦ ፓትርያርኩ ቢያጠፉ ወይም ሃይማኖት ቢያፋልሱ እራሳቸው በሰሩት ሥራ ይቀጣሉ እንጂ፤ ካህናት አባቶች ተባባሪዎች ናቸው ተብለው ለምን ይወገዛሉ?
፭፦ ቤተ-ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ስለ ፍቅር እያስተማረች፤ በእርስዎና በፓትርያሪኩ መካከል ለምን ፍቅር ጠፋ?
፮፦ ምእመኑስ፥ ለምን በቤተ-ክርስቲያን ተገኝቶ እንዳያስቀድስ ታገደ?
፯፦ ሠው በቤተ-ክርስቲያን ተገኝቶ አስቀድሶና ሥጋ ወደሙን ለመቀበል ለምን ተከለከለ?
፰፦ የጌታ ሥጋ ወደሙ በካህናት አባቶች እጅ አትቀበሉ፤ የፓትርያሪኩ ተባባሪዎች ናቸው ለምን ተባለ?
፱፦ የእናንተ የሃይማኖት አባቶች ፍቅር መጥፋት፤ ለመናፍቃን፥ በር አይከፍትም ወይ?
፲፦ ዛሬ ዛሬ መናፍቃን፦ “በእነሱ በኩል ፍቅር ጠፍቷል፣ እንደምታዩአቸው አንዱ አንዱን እየወገዘ ነው ያለ” እያሉ ይሳለቁብናል። በእርሶ በኩል ይኼን እንዴት ያዩታል?
፲፩፦ ይኽ ውግዘት የተላለፈው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ ወይስ ለአዲስ አበባ ከተማ ብቻ?
፲፪፦ ይኼን ውግዘት የተቀበሉ ቤተ-ክርስቲያኖች ስንት ናቸው፣ በውግዘቱስ አምነውበታል፤ ይኼንንም እንዲያብራሩልን?
፲፫፦ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል፤ በካህን አባቶች እጅ አትሳለሙ ለምን ተባለ?
፲፬፦ ውግዘት ከተላለፈ ወዲህ ብዙ እናት አባቶች፣ እኅት ወንድሞች ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ አሉ፣ እነዚህ ሠዎች፥ እንደተወገዙ ነው የሞቱት ወይስ ተፈተው፤ ይኼንንም እንዲያብራሩልን?
፲፭፦ ይኼ ውግዘት በግል ጋዜጣ ከማስተላለፍዎ በፊት ለምን በየቤተ-ክርስቲያኑ ተገኝተው ለምእመኑ አላስተላለፉም?
፲፮፦ ይኽ ውግዘት እስከመቼ ነው የሚቆየው፤ ለምን?
፲፯፦ ይኽ ውግዘት ከአዲስ አበባ ውጭ የሰማ ሃገር አለ? ካለ፥ ውግዘቱን ተቀብሎታል ወይንስ አልተቀበለውም?
፲፰፦ ይኽ ውግዘት ብጹዕ አባታችን ሰምተዋል ወይስ አልሰሙም?
፲፱፦ ብጹዕ አባታችን የግል ጋዜጣ ገዝታችሁ አታንብቡ ብለው አውግዘዋል፣ የእርሶ ውግዘት የተላለፈው ደግሞ በግል ጋዜጣ ነው፤ ይኼ ሊጋጭ አይችልም ወይ?
፳፦ አንዱ ያወገዘው አንዱ ሊፈታው አይችልም ወይ? ካልቻለ፥ እስከመቼ በውግዘት ውስጥ ልንኖር እንችላለን? ወይስ ከቤተ-ክርስቲያን እስከመቼ እርቆ ሳያስቀድሱ ይቆያሉ?
ለቀረበላቸው ሙሉ ጥያቄዎችና የሰጡትም እጹብ ድንቅ ምላሻቸውና መልሶቻቸው ይስሙ፤ ያዳምጡ።
ለአባታችን ሊቀ ሊቃውንት አለቃ አያሌ ታምሩ፥ ቃለ ሕይወትን ያሠማልን፤ መንግሥተ ሠማያት ያውርስልን፤ ጸጋ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ አሜን።
-----------------------------------------------------
-----------------------------------------------------
No comments:
Post a Comment