Friday, March 21, 2014

ተግሣጽን አትቀበሉምን? /ኤር 35፥13/



የክብሩ ሞገሥ፦ በሠማያት፣ በምድር፣ በጥልቁም ሥፍራ ያለ፤ እግዚአብሔር ለፈጠረን ፍጥረቱ (በተለይ ለእኛ በአምሳሉ ለፈጠረን ሠዎች) ስለሚወደንና ስለሚያፈቅረን ይገሥጸና! በነጐድጓድና መባርቅት፣ በከባድም ደመና ድምፅ፣ በብርቱ የንፋሳት ውሽንፍር ድምፅ፤ እግዚአብሔር፥ ህዝቡን ይገስጻል!።

ከነዚህ፥ ከተፈጥሮ ተግሣጽ ይልቅ ግን ተግሣጽን በአንደበተ-ቃል (ከሠዎች በሚወጣ ቃል) ሲገሥጽ በብሉይም በሐዲስም እናያለን። ለምሳሌ ያህል፥ በብሉይ፦ እግዚአብሔር፥ በሚወዳቸውና እንደ ሐሳቡና እንደ ትህዛዛቱ የሚሄዱትን አገልጋዮቹን በመላክ፣ በነቢዩ ኤርምያስ አንደበት አድሮ፦ ተግሣጽን አትቀበሉምን? /ኤር 35፥13/ እያለ ያናግር ነበር እናነባለን።

ይህ ተግሣጽ፥ በብሉይ ብቻ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳንም ቢሆን የምናገኘው እውነታ ነው! ይህ የተግሣጽ እውነታ ደግሞ እራሱ ባለቤቱ፦ የፍቅር አምላክ፣ የተግሣጽ ጌታ፣ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም በመዓክለ ምድር ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በስጋ ተወለዶ፣ (ከበረት ውስጥ መወለድ ጀምሮ እስከ በዓለ ዕርገት፤ የተተረከውን ብናነብና ብናስተውል፣ በመንፈሳዊ ዕይታ ብናያቸው፣ ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ተግሣጽ እናገኛለን! ) ሲያስተምርና ይህንን ዓለም በፍቅሩ አቅርቦ፣ በተግሣጹ ገሥጾ፤ ሕይወትን እንድናገኝ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበላቸው፦ "ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?" ብሎ ሲጠይቅ፥ ሐዋርያትም በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን፣ እንዲሁም በአይሁድ ረበናት ካህናት የሚባለውንና የሚናገሩት ቀድመው ስለሰሙ፦ "አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው፤ ይላሉ አሉት።"


በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ    ፲፮፥ ከቁጥር ፩- ፳፰ ድረስ እንመልከት፦ የፍቅር አምላክ፣ የተግሣጽ ጌታ፣ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም፥ "እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?" አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ አለው፦ "አንተ ክርስቶስ፥ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ ብሎ የማይሻረውን የንጉሦች ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ፤ አንተ ነህ አለው። በዚህን ጊዜ፥ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ "የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።" ሲል በማይሻረው በመለኮታዊ ቃሉ ለቅዱስ ጴጥሮስ "ብፁዕነቱን" አረጋግጦለታል!።

አሁን ወደተነሳሁበት ርዕስ ስመለስ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ሂድና ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ተናገር እንዲህም በላቸው። ቃሌን ትሰሙ ዘንድ ተግሣጽን አትቀበሉምን? ይላል እግዚአብሔር። /ኤር 35፥13/ እንደተባለው፥ ይኼው ቅዱስ ጴጥሮስ ከፍቅር አምላክ፣ ከተግሣጽ ጌታ፣ ከመድኅነ ዓለም ከኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ቃሉ "ብፁዕነቱን" ሰምቷልም፣ አዳምጧልም!። ቢሆን ግን አንድ ሌላ ደግሞ የሰማው ነገር አለ፤ ይሄ የሰማው ነገር ምን ይሆን?

የዓለም በግ፥ ስለራሱ እንግልትና ስቃይ፣ ድብደባና ግርፋት፣ ስቅለትና ሞት፣ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር። በዚህን ጊዜ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ፦ "አይሁንብህ ጌታ ሆይ፥ ይህ ከቶ አይደርስብህም" ሲል፤ ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ቅዱስ ጴጥሮስን፦ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።"

ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ቃሉ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ቅዱስ ጴጥሮስን "ብፁዕ ነህ" ብሎታል፤ እዚህ ጋር ደግሞ በመለኮታዊ ቃሉ፦ "ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል።" ብሎ በአንድ አረፍተ-ነገር ስለ አራት ነገሮች ሲገሥጸው እናያለን

፩ኛ፤ ወደ ኋላዬ ሂድ፦ (አገልጋዮች፥ የቱንም ያህል "ብፁዕነቱን" ደረጃን ቢቀዳጁም፤ ከክርስቶስ ኋላ እንጂ ፊት እንደማይሆኑ)

፪ኛ፤ አንተ ሰይጣን፦ (አገልጋዮች፥ በተሰጣቸው የእግዚአብሔር የጸጋ ሥጦታ በአግባቡ ካልተጠቀሙበትና ክብር ለእግዚአብሔር ካልሰጡ፤ የሰይጣን ማደሪያዎችና ማስፈጸሚያዎች እንደሚሆኑ፤ ልክ እንደ ይሁዳ ማለት ነው። ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ ተብሎ እንደተመዘገበው። ሉቃ ፪፩፥፪፩)

፫ኛ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና፦ (አገልጋዮች፥ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የነበሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ በራሳቸው አሳብ ሲመኩና ሲጠበቡ፣ እግዚአብሔር በምህረቱ ከመጠየቅ ይልቅ አሁን እያገለገሉ ባላቸው እውቀት መመካት ሲጀምሩ፤ እንደ ሠዎች ሐሳብ መመርመር ቀላል ይመስላቸውና የሠማዩን አምላክ መግቦቱንና ቸርነቱን በቀመር ለመፈለግ እንዳይኳትኑ፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ሲል ለሰው ዘር ሁሉ በተግሣጽ መልክ ተገሥጸናል።)

፬ኛ፤ ዕንቅፋት ሆነህብኛል፦ (አገልጋዮች፥ እራሳቸውን የእግዚአብሔር ቀናኢ ሠው በባድረግ፤ ዕንቅፋት የሚሆኑ ብዙዎች ናቸው። ይኽውም፦ ቅድሱ ጳውሎን የሕይወት ታሪክ መቃኘትና መዳሰስ መልካም ይመስለኛ። ቅድሱ ጳውሎስም ተገሥጿል። ሳያውቀው፥ ዕንቅፋት በመሆን ስንቱን ወጣኒ ክርስቲያናትን ለግዞትና ለምርኮ፣ ለእስራትና ለግርፋት፣ አንዳንዶቹንም ለስቃይና ለሞት ያደረሰ ሠው ነበር፤ እንደነዚህ ዓይነት ዓገልጋዮች ስለለነበሩና ስላሉ፣ ወደፊትም ስለሚኖሩ፤ ዕንቅፋት ሆነህብኛል ሲል ገሠጸው።)

ጠቢቡ ሠለሞን በምሳሌው፦ "ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር።" /፫፥፲፩/ ይለናል! ተግሣጽ የሕይወት ምዕራፍ ነው፤ ፍቅር መልካም ነው፥ ሁልጊዜ ፍቅር ከሆነ ተግሣጽ የሰማን ዕለት አይጣል ነው የሚሆነው! ወዳጄ ሆይ፦ ተግሣጽ በሰማህ ጊዜ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር!።

No comments:

Post a Comment