Showing posts with label ምልከታ. Show all posts
Showing posts with label ምልከታ. Show all posts

Monday, April 20, 2015

የምናዝነው ስንት ሰው ሲሞት ነው? ‹ሰማዕታተ ዘ ሊቢያ› ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት



በየመን፣ በደቡብ አፍሪካና በሊቢያ ስለሚሞቱት ዜጎቻችን የሚሰጡት መንግሥታዊ መግለጫዎች ሁለት ነገር የጎደላቸው ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሰብአዊ ስሜት፡፡ ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ስለሌላው ሰብአዊ ፍጡር መከራና ስቃይ ሲሰማ መጀመሪያ አንዳች የኀዘን ስሜት ይሰማዋል፡፡ ከዕውቀት ይልቅ ስሜት ለሰዎች ቅርብ ነውና፡፡ ባለሥልጣን ቢሆን፣ ፖሊስ ቢሆን፣ ዳኛ ቢሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሆን ሰው ነውና ስሜት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ያዝናል፣ ይከፋዋል፣ ልቡ ይረበሻል፣ ሆዱ ይባባል፣ ኅሊናው ይደማበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው ሥራው ማዘን ቀጥሎም ኀዘኑን በወጉ መግለጥ ነው፡፡


ሰሞኑን የማያቸው መግለጫዎቻችን ግን የኀዘን ወግ በሀገራችን የሌለ የሚያስመስሉ ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተው ለሞቱት ወገኖቻችን እንደ ኢትዮጵያዊነት ኀዘናቸው የሚገልጡት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው የምናያቸው፣ ነጠላ የሚያዘቀዝቁት ስንት ሰው ሲሞትብን ነው? የሚያስብሉ ናቸው፡፡ ኀዘንኮ ፖለቲካ አይደለም፣ ፓርቲ አይደለም፣ ርእዮተ ዓለም አይደለም፣ ሊብራልም አብዮታዊ ዲሞክራሲም አይደለም፡፡ ኀዘን ሰብአዊነት ነው፡፡ የሚመራቸው ዜጎቹ፣ የሚያሠማራቸው በጎቹ ሲታረዱና ሲሞቱ ኀዘኑን በይፋ የማይገልጥ መሪና እረኛ መቼ ነው ኀዘኑን የሚገልጠው?

Sunday, April 19, 2015

ጭንብል ለባሽ

ራሱን የሶርያና ኢራቅ እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው (ISIS) በዓለም ላይ ከሱኒ እስልምና ውጭ ያሉትን፤ እንዲኹም ደግሞ የሱኒ ሙስሊም ተከታይ ቢሆን እንኳን ዘግናኝና አስጸያፊውን ድርጊቱን የሚቃወሙትን የሱኒ ሙስሊም ተከታዮችን፤ አጠቃላይ ሃይማኖት ባለውም በሌለውም በማንኛውም የሠው ልጅ ፍጥረት ላይ ደም የሚጠጣበት ካራውን ካነሳ ቆይቷል።

ይኼ ጭንብል ለባሽ፦ ደም መጣቹ፣ ጽንፈኛና አክራሪ እስላማዊ ቡድን (ISIS) በምዕረት የለሹ ሠይፉ፥ ለክርስትና ያለውን ጥላቻ ከቃላት በላይ ነው! ለክርስትናም ብቻ አይደለም ለሌሎችም ጭምር እንጂ! ጭንብል ለባሹ፦ ደም መጣቹ፥ የክርስትና ሃይማኖት ተቋሟትንና የእምነቱን ተከታዮችን አንገት እየቀላ፣ ደም እየጠጣ፤ ክቡር ሠውን በአሰቃቂ ግድያ እየገደሉ፤ ጭንብል አጥልቀው፥ "አላህ ወክበር" የሚሉት የተለመደ ነገር ነው።

ነገር ግን ልበ አምላክ እንዲህ ይላል፦ «ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፣ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፤ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም። ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።» (መዝ ፲፬፥፮-)


ጭንብል ለባሽ፦

ማንነቱን ደብቆ፤
ጭንብል አጥልቆ፤
ሠይፍ ጎመድ ታጥቆ፤
የሠው አንገት አንቆ።

ጭንብሉ ቢገለጥ እኒያ የተከበሩ፤
እነማን እንደኾነ ይለዩ ነበሩ።

ጭንብል ትመቻለች፤
ማንነትን ትሸፍናለች፤
"አላህ ወክበር" ታሰኛለች፤
የሠው አንገት ታስቀላለች።

----------------------------------------------------------------------------
መሪር ዕንባችንና ኃዘናችን ከባድ ነው!

«ድንግል ሆይ፦ ከዓይኖችሽ የፈሰሰውን፥ በተወደደው ልጅሽ ፊት የወረደውን፣ መሪር የሆነ እንባሽን፣ ኃዘንሽን፤ አሳስቢ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ።» (ኤር ፴፩፥፲፭፤ ማቴ ፪፥፲፯-፲፰፤ /አባ ሕርያቆስ)

፲፩//፳፻፯ /
-----------------------------------------------------------------------------