Tuesday, October 15, 2013

“እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም”



(እውነት ነው እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም!!! እናሳ ከወለደች በኃላስ እንዴት አወቃት?)

አቤቱ ጌታችን ሆይ፦ ተቀዳሚ ተከታይ ስለ ሌለው ስለ ልጅህ ስለ ወደዳጅህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አማኑኤል ብለህ ይቅርታህን ከኛ አታርቅ፤ መሐላህንም አታፍርስ በእውነት ያለሐሰት።

በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልውና ሆነው የሚኖር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ። በሱም አብ መንፈስ ቅዱስ ህልውና ሆነው የሚኖሩ። ልቦናው አብ፣ ያንደበቱም ትንፋሽ መንፈስ ቅዱስ፤ የሚሆን ኢየሱስ ክርስቶስ። እርሱም የአብ የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው የሚኖር ኢየሱስ ክርስቶስ።

በልዕልና ሳለ በመሠረት ያለውን የሚያይ። በውነት ከሰማይ በቸርነቱ ወርዶ ክብርት ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን በሰው ሥጋ ተወለደ። ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ ተወስኖ፣ ልጅነትን ሰጥቶ፤ በሥጋው ወገኖቹን ያደርግ ዘንድ።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ልደቱ ነገር እንዲህ ነው፦ እናቱ እመቤታችን ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ስላት። ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመናገር፣ ከመዳሰስ፤ ድንግል ስትሆን።

ዕጮኛዋ ዮሴፍ ግን ደግ ሰው ነውና ሊገልጣት፣ ሊያጣላት አልወደደም። ሰውሮ ሊያኖራት ወደደ እንጂ! ይህንንም ሲያስብ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፣ በሕልምም ተነጋገረው።

የዳዊት ልጀ ዮሴፍ ሆይ ዕጮኛህ ማርያምን መቀበል አትፍራ። ከሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና። እነሆ፦ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም ኢየሱስ (መድኃኒት) ትለዋለች። እሱ ወገኖቹን ከኃጢአታቸው ፍዳ ያድናቸዋልና።

ይህ ሁሉ የተደረገው፥ ነቢይ ከእግዚአብሔር አግኝቶ፤ እነሆ፦ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል ብሎ የተናገረው ይደርስ፣ ይፈጸም ዘንድ ነው።

አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከኛ ጋር የሆነ ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ተነሥቶ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ። ዮሴፍም ለድንግልናዋ ሰገደ። ለንጽሕናዋ፣ ለቅድስናዋም። ተገዛ። ዕጮኛው የምትሆን ማርያምንም ወሰዳት። በኵር ተብሎ የተጠራ ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም። (ጻድቁ ዮሴፍ እመቤታችንን ድንግል ማርያም በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የመውለዷ ምስጥር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት መሆኗን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፣ አልተረዳም ነበር።) /ድርሳነ ማሕየዊ ምዕ 113-38/



No comments:

Post a Comment