Sunday, February 9, 2014

ትምህርተ ጋብቻ ክፍል፦ ፪ በመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

              ፩፡- የትዳር ጓደኛን ማን ይምረጥልን?
         የትዳር ጓደኛ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ባለጸጋ ፥ወይም ባለሥልጣን፥ ወይም ቆንጆ፥ ወይም ጤነኛ፥ ስለሆኑ ብቻ የሚሹት አይደለም። ደሀ፥ ወይም ተርታ ሰው፥ ወይም መልከ ጥፉ፥ ወይም በሽተኛ ፥ቢሆኑም የሚፈለግ የሚናፈቅ ነው። ሳያገቡ ለመኖር የወሰኑትም ቢሆኑ ፥ፍላጎቱ ያለው በአፍአ ሳይሆን በውስጥ ስለሆነ፥ ከኅሊና ውጣ ውረድ ሊድኑ አይችሉም። ስለሆነም ከኅሊናቸውና ከፍላጎታቸው ጋር እየታገሉ በገድል ይኖራሉ። በዚህ ትግል ማሸነፍም መሸነፍም ሊኖር ይችላል። የትዳር ጓደኛ ከውጭ ወደ ውስጥ የምናስገባው ሳይሆን፥ ከውስጣችን ፈልገን የምናገኘው ነው። ይህም ማለት፡- በአዳምና ሔዋን ሕይወት እንዳየነው፡- እግዚአብሔር የትዳር ጓደኞቻችንን አስቀድሞ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ አስቀምጧቸዋል። በመሆኑም አንድ ሰው ሥዕል (ፎቶ ግራፍ) ይዞ የሥዕሉን ባለቤት እንደሚፈልግ በውስጣችን የተቀመጠውን፥ የተሣለውን ይዘን መፈለግ ይገባል።

የሰው ልጅ በእምነቱም ሆነ በሌላው ነገር ሁሉ ፍጹምነት ስለሌለው በፍለጋው (በመንገዱ) አጋዥ ያስፈልገዋል። ያንንም የሚሰጠን ያለ ጥርጥር እግዚአብሔር ነው። ለዚሀም የጾምና የጸሎት ሰው መሆን ያስፈልጋል። የነቢያት አለቃ ሙሴ ጽላቱን ከእግዚአብሰሔር እጅ የተቀበለው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጾሞ ነው፥ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። ዘጸ ፴፩፥፲፰። እኛም እንደ ጽላት እንደ ታቦት ተከብረው የሚያስከብሩ የትዳር ጓደኞቻችንን በጾምና በጸሎት ልናገኛቸው እንችላለን ብለን ልናምን ይገባል። በአገራችን፡-«አቶ እገሌ እኮ ታቦት ማለት ናቸው፥ ወ/ሮ እገሊት እኮ ታቦት ማለት ናቸው፤» የሚባሉ ነበሩ። ታቦት የሚያሰኛቸው የጸና ሃይማኖታቸው፥ የቀና ምግባራቸው ነበረ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ኢተአምሩኑ ከመ ታቦቱ ለእግዚአብሔር አንትሙ፥ ወመንፈሰ እግዚአብሔር ላዕሌክሙ። እናንተስ የእግዚአብሔር ታቦት (ማደሪያ) እንደሆናችሁ፥ መንፈስ ቅዱስም አድሮባችሁ እንዳለ፥ እንደሚኖርም አታውቁምን? (አታስተውሉምን፥ ልብ አትሉምን)?» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛቆሮ ፫፥፲፮። የነቢያት አለቃ ሙሴ ጽላቱን ለመቀበል እስከ ደብረ ሲና ተጉዟል፥ አቀበቱን (ተራራውን) ወጥቷል። እግዚአብሔር የሚያሳየውን ሁሉ በትእግሥት ተመልክቷል፥ የሚነግረውንም ሁሉ በትእግሥት አድምጧል፥ የሰጠውንም በጸጋ ተቀብሏል። እኛም የምንሻውን ለማግኘት እስከ ቤተክርስቲያን በእግረ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በእግረ ልቡና ጭምር መጓዝ አለብን። (ንስሐ መግባት፥ ሥጋ ወደሙ መቀበል፥ ዘወትር ማስቀደስ፥ ቃለ እግዚአብሔርን ማድመጥ ይጠበቅብናል)። ይኸንን ሁሉ ለማድረግ አቀበት ቢሆንብንም ከራሳችን ጋር ታግለን ማሸነፍ፥ ለነገሮች ሁሉ ትእግሥተኛ መሆን ይኖርብናል።

፩፥፩፡- የትዳር ጓደኛችንን ራሳችን መምረጥ አለብን፤
ልካችንን የምናውቀው ከማንም በላይ ራሳችን ነን። ራሳችንን ካልዋሸነው በስተቀር ለዓይናችን የሚሞላውን፥ የልባችንን ሚዛን የሚደፋውን፥ በልካችን የተሰፋውን ልብስ እናውቀዋለን። በመሆኑም ጊዜው ሲደርስ በጣም ሳንቸኩል፥ እጅግም ሳንዘገይ፥ እግዚአብሔር እንዳመለከተን ልንመርጥ ይገባል። ምክንያቱም መቸኰልም፥ መዘግየትም በየራሳቸው ችግር አለባቸውና ነው። ቸኩለውም ዘግይተወም የሚቸገሩና የሚጨነቁ፥ የሚበሳጩና የሚያማርሩ፥ ተስፋ ቆርጠውም እግዚአብሔር ትቶኛል፥ ረስቶኛል፥ የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። በአገራችን፡- «የቸኰለ አፍሶ ለቀመ፥ የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል፥ የነቶሎ ቶሎ ቤት ዳርዳሩ ሰንበሌጥ፤» የሚሉ ሥነ ቃላት አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፡- እንኳን ለግብር ለነቢብ (ለመናገር) እንኳ መቸኰል እንደማይገባ ይመሰክራል። «ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፥ ለመናገርም የዘገየ (ረጋ-ያለ)፥ ለቁጣም የዘገየ ይሁን፤»ብሏል። ያዕ ፩፥፲፱። ይኸንን በተመለከተ፡- «የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል፤» የሚል ሥነ ቃል አለ። እንዲህም ሲባል በጣም መዘግየት ይገባል ማለት አይደለም። ምክንያቱም፦  ለበጎ ነገር ሲሆን ሰይጣን ሰውን ሆን ብሎ የሚያዘገይበት ጊዜ አለና። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- የኤማሁስን መንገደኞች፡- «እናንት የማታስተውሉ፥ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤» በማለት ወቅሷቸዋል። መውቀስ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ የተጻፈውን፡- ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት ትንቢት እየጠቀሰ ተርጉሞላቸዋል። ሉቃ ፳፬፥፳፭። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ሰይጣን አዘገየኝ፤» ያለበት ጊዜ አለ።

         እንግዲህ በጣም ሳንቸኵል፥ በጣምም ሳንዘገይ፡- የትዳር ጓደኛችንን እንምረጥ ስንል፡- «ስለ እኔ ማንም አያገባውም፤» በሚል መንፈስ፥ በራችንን ጥርቅም አድርገን ዘግተን አይደለም። የተዘጋ ቤት ንጹሕ አየር እንደልብ ስለማይገባው ይታፈናል። በዚህን ጊዜ ለመተንፈስ ያስቸግራል፥ ለአስምና ለተመሳሳይ በሽታዎችም ስለሚያጋልጥ ጤና ይታወካል። ለብቻው አእምሮውን ዘግቶ የሚያስብም ሰው እንዲሁ ነው። ስለዚህ አሳባችንን የምናጋራው፥ ጭንቀታችንን የምናካፍለው ሰው ያስፈልገናል። ቅዱስ ዳዊት፡- «ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር፥ ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት።» ያለው ለዚህ ነውና። መዝ ፻፲፥፲።

፩፥፩፥፪፡- የካህን ምክር፤
ካህን፡- የነፍሳችን (የሰውነታችን) አባት ነው። «በጎቼን ጠብቅ፥ ጠቦቶቼን አሰማራ፥ ግልገሎቼን ጠብቅ፤» እንዲል፡- የነፍስ የሥጋችን ጠባቂ (እረኛ) ነው። በምድር ያሰረው በሰማይ የታሰረ ነው፥ በምድር የፈታው በሰማይ የተፈታ ነው። (እነርሱ በምድር የሚሠሩትን እርሱ እግዚአብሔር በሰማይ ያጸናዋል፥ ይቀበለዋል)። ማቴ ፲፮፥፲፱፤ ፲፰፥፲፰። ካህን ኃጢአቱን ይቅር ያለው ሰው ይሰረይለታል፥ ይቅር ያላለው ግን አይሰረይለትም። ዮሐ ፳፥፳፪። ይህም በሥልጣነ ክህነት የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው። «እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ።» እንዳለ፡- እግዚአብሔር ከካህኑ ጋር ነው። ማቴ፳፰፥፳። በመሆኑም፡- በሥልጣነ ክህነት በኵል በካህኑ የሚሠራ እግዚአብሔር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፡- የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ አንድ ናቸው።. . . ስለ በጎ ፈቃዱ፥ መፈለግንም፥ ማድረግንም፥ በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።» ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፫፥፯፤ ፊል ፪፥፲፫።

         ምናልባት ከእኔ ጀምሮ የካህኑ ሕይወት እንደ ሰው ድካም ሊኖርበት ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ድካም የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳናገኝ አይከለክለንም። ይኸንን በተመለከተ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- «መሪዎቻቸው ደካሞች እመናኑ ግን ደጎች ናቸው። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋ በካህኑ ሕይወት ላይ አይመካም። ይህንንም የምለው የቄሱን ሕይወት በመመራመር ስለከበረ ትእዛዙ ማንም ሰው እንዳይጠራጠር ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ነገር የሚደረገው በምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በኵል ጸጋን በሚያድል በእግዚአብሔር ስለሆነ ነው።» ብሏል። ቅዱስ አትናቴዎስም፡- «የጥምቀቱን ውኃ የሚቀድሰው ካህኑ አይደለም፥ ነገር ግን በተሰጠው ሥልጣነ ክህነት የሚገባውን አገልግሎት ይፈጽማል፤» ብሏል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፡- «እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፤ የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን እኔ ባለሁበት አለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ለከንቱ የሆነብኝ አይደለም፤ እኔም ከሁሉ ይልቅ ደከምሁ፤ ነገር ግን በእኔ ላይ ያደረው የእግዚአብሔር ጸጋ አጸናኝ እንጂ እኔ አይደለሁም። አሁንም እኔም ብሆን፥ እነርሱም ቢሆኑ እንዲህ እናስተምራለን፤ እናንተም እንዲሁ አምናችኋል።» ብሏል። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፱። የእኛም እምነት እንዲህ መሆን አለበት።
        
         ካህኑም በተቻለ መጠን፡- «እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ፥ የክርስቶስም መከራ ምስክር፥ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎችን እማልዳቸዋለሁ። በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን። ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኃይል አትግዙ። የእረኞችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ።» የተባለውን መቼም ቢሆን መርሳት የለበትም። ፩ኛ ጴጥ ፭፥፩።

         እንግዲህ፡- የትዳር ጓደኛን በምንመርጥበት ጊዜ በተለያየ አቅጣጫ እንመለከት ይሆናል። ወይም የመረጥነው በሥጋ ፍላጎት ተሸፍነን ይሆናል። ስለዚህ ለእኛ ያልታየን ለካህኑ ሊታየው ስለሚችል፥ የራቀውን አቅርቦ እንዲያሳየን፥ የተሰወረውንም ገልጦ እንዲነግረን፥ ምክረ ካህን ወሳኝ ነው። እኛም ብንሆን፡- «ከዚህ አንጻር አላየሁትም ነበር፤» የምንለው ብዙ ነገር ስላለ ግድ ነው። ካህኑ፦ ከልምድም፥ ከመንፈሳዊነትም፥ ከማንበብም፥ ከትምህርትም ብዙ ነገር ያውቃል። ዳዊት፣ ወዳሴ ማርያም ስለሚደግም፥ ጽላት ስለሚዳስስ፥ ሥጋውንና ደሙን ስለሚፈትትም እግዚአብሔር ይረዳዋል። በኋላ ውሉ የጠፋ ችግር ይዞ ወደ ካህኑ ከመምጣት ችግሩ ሳይፈጠር በፊት አስቀድሞ መምጣቱ አማራጭ የለውም። መቼም ችግር የሌለው ትዳር ባይኖርም፡- ቢያንስ ችግሩን ማወቁ በራሱ ግማሽ መፍትሔ ነው። ዛሬ በምንመራረጥበት ጊዜ፡- «ንስሐ አባቴን ላማክር፤»ስትል፡- «ወሳኞቹኮ እኛ ነን፥ እርሳቸውን ምን አገባቸው፤» የምንል ከሆነ፡- «ንስሐ አባቴን ላማክር፤» ሲል፡- «ወሳኞቹኮ እኛ ነን፥ እርሳቸውን አይመለከታቸውም፤» የሚባል ከሆነ፡- ነገ ከነገ ወዲያ ራሳችን በቆረጥነው በትር መመታታችን አይቀርም። በትዳር ውስጥ ችግር ሲፈጠር፥ ፈተናው ሲጠነክር፥ የንስሐ አባት ነገር ሲነሣ ሰሚ ይጠፋል። ካህንን የሚንቁ ሰለጠንን ባይ ሰዎች እንኳ ማጣፊያው ሲያጥራቸው፥ ፍርድ ቤቱን ሽሽት የሚመጡት ወደ ካህኑ ነው። ያን ጊዜ፡- «አንተ ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው፥ አንቺ ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው፤»በሚል እርስ በርስ አይደማመጡም፥ አይተማመኑም። እንዲህ እንዳይሆን ነው፥ «የዋሃን ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና፤ (በምክረ ካህን፥ በፈቃደ ካህን የሚኖሩ ንዑዳን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና)፤» እንደተባለ፡- ምክረ ካህን ያስፈልጋል የተባለው። ማቴ ፭፥፭። በካህን አድሮ፥ ከካህን ጋር ሆኖ የሚመክረን እግዚአብሔር ነውና። በመሆኑም የካህኑን ምክር ማድመጥ ይገባል። አለበለዚያ፡- «ምክሬን ናቃችሁ፥ ዘለፋዬንም አልተመለከታችሁም፤» ብሎ እግዚአብሔር ይወቅሰናል። ምሳ ፩፥፳፭።

፩፥፩፥፫፡- የቤተሰብ ምክር፤
         ቤተሰብ ሲባል አባትን፥ እናትን፥ ወንድምን፥ እህትን ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም አጎትን፥ አክስትን፥ የአክስት የአጎት ልጆችን ሊያጠቃልልም ይችላል። ነገር ግን የሠላሳ ሰው ሚዛኑ ሠላሳ ስለሆነ መጠንቀቅንም ቸል ሳንል ነው። ምክንያቱም ለአንዱ የሚጥመው ለሌላው ሊመርረው ይችላልና። ስለዚህ ሰው አብዝተን፥ የትዳሩን ምርጫ የቀበሌ ምርጫ እንዳናደርገው መፍራት አለብን። እርግጠኛ ነኝ፤ የሚበዛው ሰው የሚያስጨንቀው፡-የመልክና የደም ግባት ወይም የዘር ወይም የሀብት ጉዳይ ነው። በመሆኑም፡- ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸውን፥ መንፈሳዊነት የሚጸናባቸውን ሰዎች መርጦ ማማከር ያስፈልጋል።

         በተለይም ወላጆች ምንም ቢሆን ለልጆቻቸው መጥፎ አይመኙም። ይሁን እንጂ ይህ በጎ ምኞታቸው በሌላ ነገር እንዳይጋረድ፡- መጋረጃውን ከፍቶ በግልጥ መወያየት ያስፈልጋል። ወላጆችም፦ እነርሱ ከነበሩበት ዘመን አንጻር ብዙ የተለወጠ ነገር መኖሩን አምነው ዘመኑን መዋጀት ይጠበቅባቸዋል። ወንድምና እህትን አቃቂር ማውጣቱን፥ ጠጉር መሰንጠቁን ትተው፥ ከወንድማቸው ወይም ከእኅታቸው ፍላጐትና አቅም አንጻር፡- መሠረታዊው ነገር ላይ ማተኰር አለባቸው። የራስን ሰው ወርቅ፥ የሌላውን መዳብ ማድረግ ግብዝነት ነውና። ሁሉም ሰው ምንም ይሁን ምን፥ ለቤተሰቡ ወርቅ ነውና። ምንጊዜም ቢሆን ለምክር በቀረበው ሰው ፍላጎት ላይ ተመሥርተን ምክራችንን መለገስ እንጂ፦ የዚያን ሰው ፍላጐት ደምስሰን እኛ እንዲሆን የምንፈልገውን ብቻ ማንጸባረቅ የለብንም። ምናልባት ምርጫቸው ስሕተት ሊኖረው ወይም ፍጹም የተሳሳተ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም፦ በተረጋጋ መንፈስ ደግሞ ደጋግሞ መምከር እንጂ በማራከስና በማንቋሸሽ፥ በማጣጣልና በማብጠልጠል ሰውን እልህ ውስጥ መክተት የለብንም። ለምክር የቀረብንም ሰዎች፥ አመጣጣችን እኛ ያሰብነውን እንዲያጸድቁልን ብቻ ኅሊናችንን ዘግተን መሆን የለበትም። ከተለያየ አቅጣጫ የሚነገረንን ሁሉ ለመቀበል ፈጽሞ የተዘጋጀ ልቡና ያስፈልገናል። በተለይም ወልደው፥ ደክመው፥ ያሳደጉንን፥ ለቁም ነገርም ያበቁንን ወላጆች ከማንም በላይ ልናደምጣቸው ይገባናል። ምክንያቱም፡- «እግዚአብሔር ፡- አባትን በልጆች ላይ አክብሯልና። የእናትንም ሥልጣን በልጆችዋ ላይ ከፍ አድርጓልና። አባቱን የሚያከብር በልጆቹ ደስ ይለዋል፤ በሚጸልይበትም ቀን ፈጣሪው ይሰማዋል። አባቱን የሚያከብር ልጅ ዕድሜው ይረዝምለታል። እግዚአብሔርን የሚሰማ ልጅ እናቱን ያሳርፋታል።» ይላል። ሲራ ፫፥፪-፯።

         ጥንት ለልጆቻቸው ሚስት የሚመርጡት ወላጆች ነበሩ። ያንንም የሚያደርጉት ብዙ አስበውበት ነው። ከልጃቸው ጠባይ ጋር የምትገጥመውን አጥንተው፥ ሃይማኖቷንና ምግባሯን መዝነው፥ ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን ብለው ነው። ከእግዚአብሔር በታች በልጆቻቸው ላይ ይህን ያህል ሥልጣን የነበራቸውን ወላጆች ለምክር እንኳ ቦታ ልንነፍጋቸው አይገባንም። አብዛኛውን ጊዜ እነርሱ የሚሉን ሁሉ የሚገባን በኋላ ነውና። በእድሜ እየበሰልን፥ በኑሮ እየታሸን ስንሄድ ይሉን የነበረው ሁሉ፡- ትክክል እንደሆነ ፍንትው ብሎ ይታየናል። «አባዬ እንዲህ ብሎኝ ነበረ፥ እማዬም እንዲህ ብላኝ ነበረ፤ ነገር ግን አልሰማኋቸውም።» ማለት እንጀምራለን። በትዳር ጓደኛ ምርጫ ላይ ብቻ ሳይሆን በኑሯችን ሁሉ የወላጆች ምክር ለሕይወታችን ቅመም ነው።

         በሌላ በኵል ግን፡- ሚዛን የሚደፉ ምክንያት ሳይኖር፡- «ምን በወጣህ የኔ ልጅ እሷን የምታገባው፥ ምን በወጣሽ የኔ ልጅ እሱን የምታገቢው፤» በሚል ትዕቢት የተያዙትን መስማት አይገባም። እንደነዚህ አይነት ሰዎች በአብዛኛው ሚዛናቸው ዘር ወይም፥ሀብት ነው። ብዙ ሀብት ይኑረው እንጂ ለሰይጣንም ቢሆን ልጃቸውን ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም። ከዘራቸው ውጪ የሆነ ሰው ልጃቸውን ከሚያገባ፥ ዘራቸው ይሁን እንጂ ጭራቅም ቢሆን ይሰጡታል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት ሀገር ቤት እያለ፡- በታክሲ ወደ ቤት ሲገባ ሁለት ወጣት ሴቶች ስለ ጋብቻ ሲያወሩ ጆሮውን ጣል አድርጎ ያደምጣቸው ነበር። የሚያወሩት ስለ ጓደኛቸው ሠርግ ነበር፤ ይህች ጓደኛቸው ያገባችው ሀብታም ነጋዴ ነው። በጨዋታቸው መካከል አንደኛዋ፡- «የሆነስ ሆነና ያገባችው የእኛን ዘር ነው?»  ብላ ስትጠይቃት እንዳልሆነ ይነገራታል። በዚህን ጊዜ፡- «ምን ነካት? ከዘሯ ውጪ እንዴት ታገባለች? ሀብቱን አይታ ነው አይደል? እኔ ብሆን፥ የዘሬን ቆማጣ ባገባ እመርጣለሁ፤» ትላለች። ይህች ልጅ ባጋጣሚ ተሰምታ እንጂ፥ በሁላችንም ልቡና ያለውን እግዚአብሔር ቢገልጥብን ከዚህ የሚተናነስ አይደለም። ስለዚህ ከቤተሰብ ጋር በምንማከርበት ጊዜ ስንዴውን ከገለባው እየለየን መሆን አለበት። አለበለዚያ ነገራችን ሁሉ እግዚአብሔር የማይቀበለው የቃየል መሥዋዕት ይሆንብናል። «እግዚአብሔርም. . . ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፤» ይላል። ዘፍ ፬፥፭።

፩፡፩፥፬፡- የባልንጀራ ምክር፤
         መልካም ባልንጀራ፡- ከወንድም በላይ ነው። «ነገር ግን ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።» እንዲል፡- እንደራሱ አድርጎ ይወድደናል። ዘሌ ፲፱፥፲፰፣ ማቴ ፲፱፥፲፱።  «ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤» እንደተባለ ፍቅሩም አክብሮቱም ይኖራል። ሮሜ ፲፪፥፱። እንግዲህ ባልንጀርነት መሆን ያለበት እንዲህ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰው ለባልንጀራው ማድረግ የሚገባውን ሲናገር፡- «አሁንም በክርስቶስ ደስታ፥ ወይም በፍቅር የልብ መጽናናት፥ ወይም የመንፈስ አንድነት፥ ወይም ማዘንና መራራትም በእናንተ ዘንድ ካለ፡- እርሱን ብቻ ታስቡ ዘንድ፥ አንድ ልብና አንድ ምክርም ሆናችሁ፥ በፍቅር ትኖሩ ዘንድ ደስታዬን ፈጽሙልኝ። በክርክርና ከንቱ ውዳሴን በመውደድ አትሥሩ፤ ትሕትናን በያዘ ልቡና ከራሳችሁ ይልቅ ባልንጀራችሁን አክብሩ እንጂ አትታበዩ። ለባልንጀራችሁም እንጂ ለየራሳችሁ ብቻ አታስቡ። ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንዳደረግልን ይህን አስቡ።» ብሏል።ፊል ፪፥፩-፭።

         ከመልካም ባልንጀራ ልቡና መልካም ነገር ይወጣል፥ በአንደበቱም በጎ ነገር ይነገራል። ስለዚህ ሁልጊዜ ከእርሱ የምንማረው በጎ ነገርን ብቻ ነው። ይኽንን በተመለከተ፡- ቅዱስ ዳዊት፡- «ምስለ ጻድቅ ትጸድቅ፥ ወምስለ ብእሲ ንጹሕ ንጹሐ ትከውን፥ ወምስለ ኅሩይ ኅሩየ ትከውን። ከጻድቅ ሰው ጋር ጻድቅ ትሆናለህ፥ ከቅን ሰው ጋርም ቅን ትሆናለህ፥ ከንጹሕም ሰው ጋር ንጹሕ ትሆናለህ፤» ብሏል። መዝ ፲፯፥፳፭። ቸር የተባለው፡- ንጽሐ ሥጋን የያዘ ሰው ወይም ወጣኒ ነው። ንጹሕ የተባለው፡- ንጽሐ ነፍስን የያዘ ሰው ወይም ማዕከላዊ ነው። ቅን የተባለው ደግሞ ንጽሐ ልቡናን የያዘ ሰው ወይም ከፍጹምነት የደረሰ ነው።

መልካም ባልንጀራ በምክሩ ከኃጢአት ይጠብቃል፥ ከሞትም ያድናል። የንጉሡ የሳኦል ልጅ ዮናታን የብላቴናው የዳዊት ወዳጅ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፬፥፵፱፣ ፩ኛ ዜና ፰፥፴፫። ብርቱ የጦር አለቃና ጀግና ነው፥ በጦር ሜዳም ድል ይቀዳጅ ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፫፥፪፣ ፲፬፥፩-፳፫። ከዚህም የተነሣ ሕዝቡ በፍቅር ያከብሩት ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፲፬፥፴፰-፵፮። የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር በፍጹም ፍቅር የታሰረች ነበረች። «እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ለሳኦል መንገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፤ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፤ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልፈቀደለትም። ዮናታን እንደ ነፍሱ ስለወደደው ዮናታንና ዳዊት ቃል ኪዳን አደረጉ። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን፥ ሰይፉንም፥ ዝናሩንም ለዳዊት ሸለመው።» ይላል። ፩ኛ ሳሙ ፲፰፥፩-፬። ንጉሡ ሳኦል ለልጁ ለዮናታንና ለብላቴኖቹ ሁሉ ዳዊትን እንዲገድሉ ሲነግራቸው የዮናታን ፍቅር አልተለወጠም፥ ለአባቱም አላደላም። እንዲያውም፡- «አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ፈልጎአል፤ አሁን እንግዲህ ለነገው ተጠንቅቀህ ተሸሸግ፤ በስውርም ተቀመጥ። እኔም እወጣለሁ፤ አንተም ባለህበት እርሻ በአባቴ አጠገብ እቆማለሁ፤ ስለ አንተም ለአባቴ እነግረዋለሁ፤ የሆነውንም እነግርሃለሁ።» እያለ ይመክረው፥ ያጽናናውም ነበር። በአባቱም ፊት ቆሞ፡- «እርሱ አልበደለህምና፥ ሥራውም ለአንተ እጅግ መልካም ሆኖአልና፥ ንጉሡ ባሪያውን ዳዊትን አይበድለው፤ ነፍሱንም በእጁ ጥሎ ፍልስጥኤማዊውን ገደለ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ታላቅ መድኃኒት አደረገ፤ እስራኤልም ሁሉ አይተው ደስ አላቸው፤ በከንቱ ዳዊትን ትገድለው ዘንድ ስለምን በንጹሕ ደም ላይ ትበድላለህ?» ብሎ ስለ ዳዊት ተከራከረ። ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ «ሕያው እግዚአብሔርን! ዳዊት አይገደልም፤» ብሎ ማለ። ፩ኛ ሳሙ ፲፱፥፩-፮። ዮናታንም ዳዊትን ከሳኦል ቁጣ ሊያድነው በስውር አሰናበተው። ፩ኛ ሳሙ ፳፥፩-፵፪። ሊያጽናናውም ዘወትር በስውር ይጐበኘው ነበር። ፩ኛ ሳሙ ፳፫፥፲፮-፲፰። በመጨረሻም ከአባቱ ከሳኦል ጋር ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ሲወጋ ሞተ። ፩ኛሳሙ ፴፩፥፪-፲፫። ዳዊትም ባልንጀርነቱን፥ ጀግንነቱን አስታወሶ አለቀሰለት፥ ቅኔም ተቀኘለት። ፪ኛ ሳሙ ፩፥፳፪።

  እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ፦ ይቀጥላል .....

9 comments:

  1. newcrack.co/xlstat-crack
     with over 200 diverse statistical instruments and characteristics for simple investigation and re-formation your data along with ms-excel; it's but one on advance five apps.
    new crack

    ReplyDelete
  2. Adobe Audition CC Crack is a program that assists individuals with further developing their composing abilities. It has been generally welcomed by PC clients who have viewed it as a compelling instrument in further developing exactness and speed.

    ReplyDelete
  3. DriverMax Pro Crack


    From this link you can get software free for lifetime.

    ReplyDelete