ይኼንን ርዕስ የተናገረውና “ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች” ያለው ፃድቁ ኢዮብ ነው። ፃድቁ ኢዮብ በክፉ በሽታና በጽኑ በተከዘ ጊዜ፥ ሦስቱም
የኢዮብ ወዳጆች የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት እንደመጡ ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይተርክልናልም፣ ተጽፎም እናነባለንም።
ቢኾንም ግን ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች በትንሹ ሐዘኑን ሊጋሩት ሞከሩ፣ ነገር ግን እስከ-መጨረሻው ሐዘኑን ሊጋሩት አልቻሉም። የኢዮብን፥
ሐዘኑን ሊጋሩት የመጡት ሰዎች እንኳን ከልባቸው ሊያዝኑለት ይቅርና ሌላ የሐዘን ቁስል እንደጨመሩበት፣ ከማጽናናትም ይልቅ፥ እንዳይጽና በቁስሉ ላይ ሌላ ቁስል ጨመሩበት፣ የኢዮብን፥
ብርታቱንና የጥንካሬውን እንዲሁም
የፈሪሐ-እግዚአብሔሩቱን ውጤት ፍሬ-አልባ ለማስመሰል ያደረጉት
ጥረት በፃድቁ ኢዮብ ዘንድ ዋጋ የለውም ነበር። ሦስቱ
የኢዮብ ወዳጆቹ ከንቱ ውትወታ፤ በፃድቁ ኢዮብ ዕይታ ሲታዩ እንዲህ ይገልፆቸዋል፦ "ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥
ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች" ይላቸዋል።
በምሥጢር ቃል ማምጣታቸውና ጆሮውም ሹክሹክታቸውን መስማቱ፤ ለመጣበት ፈተና በብቃት
ማለፍና ለመንፈሳዊ ተጋድሎውና ለሕይወቱ መቅረዝ እንዳደረገው እንመለከታለ። ወደ ታች ወረድ ሲል ደግሞ “የዝምታ ድምጽ ሰማሁ”
ይላል። (ኢዮ ፬፥፲፮)
በዝምታ ድምጽ ውስጥ ብዙ መልእክት አለ! ነቢየ ኤልያስም በዝምታ ድምጽ ውስጥ ነበር
እግዚአብሔር የተገለጠለት። እነሆም፦ “በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፣ ዓለቶቹንም
ሰባበረ፥ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ
ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላም እሳት ሆነ፥ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥም አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ፥ ትንሽ
የዝምታ ድምፅ ሆነ። በዚህ
በዝምታ ድምፅ ነበር የእግዚአብሔር ድምጽ የተሰማው።
(፩ኛ ነገ ፲፱፥፲፪)
ዛሬ ዛሬ ከሃገራችን ኢትዮጵያ መንግስት
ጀምሮ በዓለም ሃገራት መንግስታት ላይ ጆሮዎቻችን ሹክሹክታውን እየሰማች ነው፤ እነዚህ መንግስታት በትረ-መንግስታቸውን እንደጨበጡ ሃገሪቷን በትንሹ ከሐዘኗ ሊጋሩት ሞከሩ፣ ነገር ግን እስከ-መጨረሻው ሐዘኗን
ሊጋሩት አልቻሉም፤ ለዚህም ነው እንደ ኢዮብ ወዳጆች ሌላ በቁስል
ላይ ቁስል እያደረሱ ያሉት። ቅሉ ግን ንቃተ-ሕሊና ያለው ሃገር ወዳድ ሕዝብ ነውና ነገሮቹን በአርምሞ ይመለከታል፤ ሕዝብም ልክ እንደ ፃድቁ ኢዮብም "ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች" እያለ በትዝብትና
በቅንነት መንፈስ ይከታተላቸዋል።
እነርሱ ግን (መንግስታት) እራሳቸውን ለዚህ ለሚመሯት ሕዝብና ለአንድ
ሃገር
አሳቢና ተቆርቋሪ በማስመሰል፣ ሌሎች ለሃገራችን እንቆረቆራለን፣ ለሕዝባችን ይገደናል፤ የሚሉትን የሕብረ-ተሰእቡን ቅን
አስተዋጽዎ የሚያበረክቱትን ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ማዋከብና ሕዝብም ለሃገሪቷ የዕውቀት ምንጭና ንቃተ-ሕሊናውን እንዳይኖረው
ለመገደብ በሥም ላይ ሌላ ሥም፣ በሕግ ላይ ሌላ ሕግ እያረቀቁና እያወጡ፤ የሕዝቡን በክፉ በሽታና በጽኑ መተከዘ (ነፃነቱን ሲነፍጉትና ሕሊናው ሲገደብበት) ግድ አይላቸውም።
ለዚህም
ነው የዓለማት ነገሥታት፥ የሕዝባቸውን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ ሲያቅታቸውና በሠላም ማስተዳደር ሲሳናቸው የሚወስዱት
እርምጃ፦ ሕዝብ ለሕዝብ በነቆራና በጥላቻ እንዲተያይ ማድረግ፣ ሕዝቡ ነፃነቱን ተጠቅሞ
ከመናገርና ከመፃፍ እንዲቆጠብ ማድረግ፣ ለሚመጣው ትውልድ ዕቅድና ንድፍ ያለው ሠላማዊ ሃገር ከማስረከብ ይልቅ እነርሱ እስካሉ
ድረስ ብቻ ሃገር እንደሚኖር መለፍለፍ ዋና ዋና ዓላማቸው ነው።
ይኼም አልበቃ ካላቸውም ምድርን በሚያናውጽ፣ ተራራዎችን በሚያንቀጠቅጥ፣ አለቶችን በሚሰነጣጥቅ፣ መትረየሶችንና
ቦንቦች ይጠቀማሉ፤ በእነዚህ፥ ምድርን በሚያናውጽ፣ ተራራዎችን
በሚያንቀጠቅጥ፣ አለቶችን በሚሰነጣጥቅ፣ መትረየሶችንና ቦንቦችን መጠቀም ግን የተረጋገጠ ሠላምና ነፃነት አይሰፍንምም፤ አይመጣምም!። “እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር ዳኛ (መንግስት)” ሲኾኑ ደግሞ እንደ ሶርያ መንግሥትና
ሕዝብ ይኾናሉ። (ሉቃ ፲፰፥፪) አምላክ ሆይ፦ከዚህስ ክፉና ጭካኔ ሠውረን!።
ሠላም ሊመጣ የሚችለው፦ መንግሥታት ይኹኑም የሃይማኖት መሪዎች፤ የሕዝባቸውን መሠረታዊ
ጥያቄ በ"ዝምታ ድምፅ" ውስጥ ሰምተውና አዳምጠው (በአርምሞ፥ በጥልቀት አስበውና አሰላስለው) ሠላማዊ ምላሽ ሲሰጡ ብቻ ነው!።
ሕዝብ፥ ፍትሕ ከተጓደለበት፣ መብቱ ከተነፈገው፣ ከዓደባባይ ሠልፍ ይልቅ በሕሊናውና በልቡ
ከታይታ ሠልፍ በላይ ያካሂዳል። ስለዚህም፦ "የሰው ብሶት በአንደበቱ ባይናገር ፊቱ፣ ኑሮው፣ ሕይወቱ ይናገራል። በዝምታ ይጮኻል። በዝምታ ያለቅሳል። በዝምታም
አቤ…..ት ይላል።" (ዲ/ን ኤፍሬም
እሸቴ)
No comments:
Post a Comment