Friday, October 2, 2015

በመልአከ መንክራት ግርማ ወንዱሙ ላይ ማጉረምረም ለምን? ክፍል ፫



በክፍል ሁለት ላይ ያቆምነው፦ «ስለ ከንቱ ውዳሴ እና ከከንቱ ውዳሴ ስለ ለማምለጥ» ነው፤ ካቆምንበት ስንቀጥል፦ እርግጥ ነው ማንኛውም ምዕመን ውዳሴ ከንቱ ከመስጡት መቆጠብ አለበት፣ እንዲሁም ደግሞ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልጋይ ስለ መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሲል ከውዳሴ ከንቱነት እራሱን መጠብቅ ግድ ይላል!፤ ይህ ታዲያ የሚሆነው በምዕመናን ዘንድ ይሁን በአገልጋዮች ዘንድ የመንፈሳዊነት ልዕልና ሲኖር ነው። በዚሁ «ስለ ከንቱ ውዳሴ እና ከከንቱ ውዳሴ ስለ ለማምለጥ» ስንነጋገር መምህር ግርማ፦ «እኔ አዳኝ አይደለሁም፥ ነኝ ብዬ ተናግሬ፣ ተመፃድቄም አላውቅም፤ አገልግሎት እየሰጠሁ እንጂ! የሚፈስና የሚያድው እግዚአብሔር አምልክ ነው!።» ያሉትን እናስታውስ።

ደግሞም ሁሉም መምህራን፥ ስለ መተተኞች፣ ስለ ጠንቋዮች፣ ስለ ድግምታሞች፣ ስለ ዛር መንፈሶች፣ አጠቃላይ ስለ አጋንት ሥራዎች መኖር ያውቃሉ፤ ስለነዚህ የአጋንት ሥራዎች እንዴት ማስቀረትና ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዴት እንደሚመልስ በትምህርታቸው ውስጥ ይሰጣል፤ ቢሆንም ግን አሁን ስለምንነጋገርበት ወደ ጠንቋይና ወደ ቃልቻ ቤት የሚሄደንው፣ ሥራውን በመተትና በጥንቆላ የሚተዳደረውን ወደ እግዚአብሔር ቤት ፊቱን እንዲመልስ እያደረጉ ያሉትን አባት መምህር ግርማን መቃወም ምን የሚሉት ነገር ነው? ደግሞስ እኚሁ አባት፥ ካህናት መብላት ያለባችሁ ቅልጥም ጠንቋዩ እንዳይበላው፣ ካህናት መጠጣት የነበረባችው ጠጅ ጠንቋዩ  እንዳይጠጣው፣ ሕዝቡን እየሰኩ እያስቀሩ፣ ሕዝቡን ፍትፍቱን ወደ ጠንቋይ ቤት መውሰዱን እንዲያቆም እና ወደ ካህኑ እንዲያመጣው እያደረጉ ያሉ አባት ናቸው። ቤተ ክርስቲያንንም በማሳነጽ ረገድም የበኩላቸውን ድርሻ እያደረጉ ነው። እንደውም ስለ ቤተ ክርስቲያንን ማሳነጽ መጋቢ አእላፍ መክብብ አጥናው ያሉትን እናጢነው።


በሸገር ሬድዮ የጨዋታ እንግዳ ተጋባዥ መጋቢ አእላፍ መክብብ አጥናው ከመዓዛ ብሩ ጋር ሲጨዋወቱ ስለ ልመና ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፦ «ቤተ ክርስቲያን የሚሰሩ (የሚያገለግሉ) ሠዎች ወንጌል ሰብከው አስተምረው አስተባብረው መስራት ሲችሉ ቃጭል እያቃጨሉ በየመንገዱ ሥዕል ይዘው የሚያካሄዱት ልመና በእውነቱ በጣም አስጸያፊ፣ ቤተ ክርስቲያንንም ሀገርንም የሚያሰድብ ነው። ይህንን ሲኖዶስ አያውቅም፤ ሲኖዶሱ ለምኑ ብሎ አልፈቀደመ። ግን ይሄንን የሚሰሩ የውስጥ ሰራተኞች ምናልባትም በጉቦ እየተደለሉ ሊኾን ይችላል፤ ፍቃድ የሚያገኙበት እንጂ ይሄ ልመና በቤተ ክርስቲያናችን በሲኖዶስ የተወሰነ ነገር አይደለም። ሲኖዶስ የሚያውቀው አይደለም፤ በቤተ ክርስቲያን ሊመካኝ አይችልምና ይሄንን በእውነቱ መንገዱን መምራት ያስፈልጋል። ወንጌልን ሰብከው ነው እንጂ ቤተ ክርስቲያን መስራት ያለባቸው ተለምኖ  አይደለም!። ደግሞ ለምነውስ የለመኑት ገንዘብ በሥራ ላይ መዋሉ ምን ዋስትና አለ? መና እንደ ሥራ፣ እንደ መተዳደሪያ ኾኗል እና በቤ ክርስቲያኒቱ የራሷን ካህናት ሆነ መነኮሳት የምታስተዳድርበት በቂ ሃብት አላት፤ የተፈጥሮ ሃብት አላት፥ ያንን ሙያዊ ሥልጣኔ /Technology/ ማሰማመርና መልክ እንዲኖረው አድርጎ፣ እንዲዳብር አድርጎ በእርሻውም እራስን ችሎ ሌላውን ለመርዳት መዘጋጀት ያስፈልጋል።» ያሉት ድንቅ አባባል መምህር ግርማ ቤተ ክርስቲያንንም በማሳነጽ ረገድም የበኩላቸውን ተሳትፎ  እያደረጉ እንደኾነ  እንገነዘባለን።

ውድ የምናከብረውና የምንወድው ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፦ በተራ ቁጥር 3 ላይ ያሰቀመጠው ሐሳብ፦ «በዘመኑ አጥማቂዎች ዘንድ የምናየው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ በክርስቶስ ስም የማይወጣው ሰይጣን የቅዱስ ሚካኤልን ስም ሲጠሩበት ይወጣል፡፡ በክርስቶስ ስም የሚያሾፍ ሰይጣን የድንግል ማርያምን ስም ሲጠሩበት ተቃጠልኩ ይላል፡፡ ይኼ ፈጽሞ ክህደት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ትምህርት አይደለም፡፡ ‹‹በስመ ሥላሴ እቀጠቅጥ ከይሴ›› ብላ ያስተማረች ቤተ ክርስቲያን ላይ ‹‹በክርስቶስ ስም አንወጣም፣ በማርያም ስም ግን እንወጣለን›› እያለ አጋንንት ወጣ የሚል ትምህርት ማስፋፋት ክህደት ነው፡፡» ተብሎ የተጻፈው ጹሑፍ መምህር ግርማን ይመለከታቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱ ደግሞ መምህ ግርማ፦ ስለ ፃድቃን፣ ስለ መልአክት ተራዳኢነት፣ ስለ ቅዱሳን በረከት፣ ስለ ድንግል ማርያም ክብር በብዙ መልክ አስተምረዋል፤ ይህም ያስተማሩት ትምህርት ወንድማችን ዲያቆን ዳንኤል በተራ ቁጥር 3 ላይ ያሰፈረው ሐሳብ በፍጹም አይመለከታቸውም።

ቢሆንም ግን ለእኔ በተራ ቁጥር 3 ላይ ያሰቀመጠው ሐሳብ፦ ልክ መናፍቃን እንደሚሉን አይነት ኾኖብኛል፤ ጥያቄም እንድጠይቅ ያስገድደኛል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስምና በቅዱሳን ስም ሰይጣን አይቃጠልም ማለት ነውን? በእነዚህ በእግዚአብሔር አገልጋዮች በቅዱስ ሚካኤል ስምስ አጋንት አይገሰጽም ማለት ነውን? ይሄንኑስ መናፍቃን ይሉት አይደለንም? ይሄ የቀረበው ሐሳብ ለመናፍቆች የሚመች አይመስላችሁንም??? የቱ ክርስቶስ ነው የሚሾፍበት? መናፍቃን አማላጅ የሚሉትን ነውን ወይንስ ሙስሊሞች መሲህ የሚሉት? እኛ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቶስን እንዲህ  ብላ እንጠራዋለን፦ ክብሩ ይስፋና፥ አዶናይ፣ አልፋና ዖሜጋ፣ አማኑኤል፣ የታረደው በግ፣ የዳዊት ልጅ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ የድንግል ልጅ፣ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው። ቤተ ክርስቲያን ስለክርስቶስ ያስተማረችን እንዲህ ነው!።

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያናችን ያስተማረችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበ፣ በትውፊትና በትርጓሜ ያለ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ቃሉስ፦ ለቅዱሳን መላእክት እንዲህ ይል አይደል ወይ? እግዚአብሔር አምላክ ለወዳጆቹ እንዲህ ይላል:- «በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።» /ዘጸ 23 20-21/ ልብ በሉ!። እግዚአብሔር መልአኩን በፊታችን ሲልክ ምን ምን ማድረግ እንድሚጠበቅብን ሲያስጠነቅቀን:- በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ «ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ» ብሎ ነው ያስተማረን። በመጽሐፈ መሣፍንት ደግሞ የሶምሶን አባት ማኑሄ ለሚስቱም፦ መልአኩን ስለማየቱ "እግዚአብሔርን አይተናልና ሞት እንሞታለን" /13 23/ ነው ያላት። በእርግጥ ማኑሄ እግዚአብሔር አይተናልና ሞት እንሞታለን ለምን አለ? መልአኩን አይተናልና ለምንስ አላለም? በተጨባጭ ይህ የሚያስረዳን ነገር የእግዚአብሔርን መልአክቶቹን ከሥልጣናቸውና ከሥማቸው የተነሳ በስማቸው ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ስላለ እግዚአብሔርን አይተናልና ብለው መስክረዋል።

ይህንንም ለማረጋገጥ ካስፈለገን የሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ቃል በሰማች ከንግግሩ "ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?" ባለች ጊዜ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስም ውስጥ የእግዚአብሔር ስም ስላለ ከትህትናው የተነሳ በጣም ተደነቀች። /ሉቃ 1 26-38/ ስለዚህ ይህ የትህትና መንፈስ ደግሞ የእግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ደግሞ በመልአክቶቹ አድሮ ያናግራል፣ ይታያል፣ ሥራውን ይፈጽማል፤ ስሙም በመልአክቶቹ ውስጥ ስለሆነ በመንገዳች ይጠብቁን ዘንድ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀው ስፍራ ያገቡን ዘንድ፥ እነሆ፥ እርሱ ከፊታችን መልአክቱን ይላክልን።

በቅዱሳን መላእክት ላይ ያለ' ስም የእግዚአብሔር ስም አይደል እንዴ? አባቶቻችንስ ሲያስተምሩን ስለ መልአክት የእግዚአብሔር ስም እንዳለበት ነው። ለዚህም ነው እንዲህ የሚሉት፦ ሚካኤል ማለት ማለት መኑ ማለት ከመ ኤል ማለት አምላክ ማለት ሲሆን በአንድነት ሲነበብ መኑ ከመ አምላክ (እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው) ማለት ነው ይህ ታላቅ መልአክ ዮሐንስ ወንጌላዊ በዕራዩ ‹‹በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ›› ብሎ ከተናገረላቸው መላእክት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን የሰባቱም ሊቃነ መላእክት አለቃ እንዲሆን እግዚአብሔር መርጦ ሹሞታል። እንግዲህ የመላእክት ስም ላይ የእግዚአብሔር ስም እንዳለበት ልብ በሉ። ስለዚህ መምህር ግርማ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚሾፉ ሳይኾኑ በሥላበ ስም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ በቅድስ ድንግል ማርያም ስም እና በቅዱስ ሚካኤል ስም፤ አጋንትን የሚገስጹ ናቸው እንጂ።

ይቆየን፤ ይቀጥላል . . .  

3 comments:

  1. ክፍል አንድ

    ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መምህር ግርማን ያተኮረ እና የሚያመሰጥር እይታው የተፃፈ መልስ

    እርግጠኛ ነኝ ይህ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የፃፈው በይበልጥ ለመምህር ግርማ መፃፉን እገነዘባለሁ። ይህ የመልስ ጽሁፍ ብዙ ሐሳዊያን ስላሉ ፣ባህታዊያን ነን ብለው ብዙ ችግር የሚፈጥሩትን የሚያታልሉትን በድጋፍ መልክ አይወክልም ። ወንድማችን በሐሳብህ እነሱን ብለህ ከሆነ በጣም ጥሩ ነው ጥሩ ብለሐል በርታ ... ነገር ግን እንደምረዳውም እሳቸውን መምህር ግርማ የሚያጠቁም መሆኑን ስለተረዳሁ ይህን ጽፌልሀለሁ :: ይህ ጽሁፍ ስለ መምህር ግርማ እና በንጹ መንፈስ ለሚያገለግሉ ሁሉ ነው
    ለእይታዎችህ በየተራ ቁጥሩ መልስ ለመስጠት ያህል :-

    ቁ1/ A/ መምህርን እንድታውቃቸው ያህልትንሽ ልንገርህ ብዙዎቻችን አንተም ሳትወለድ በፊት
    A.1/ መምህር ግርማ ዲያቆን ሆነው ለረጅም አመታት በባሌ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በምግባር በታዛዝነት በጽናት እግዚአብሔርንና ቤተክርስቲያንን ምእመንን አገልግለዋል
    A.2/ እንደማንኛውም ሰባኪ ለዘመናት ከዲቁና ጀምሮ እግዚአብሔር እንደገለጠላቸው ህዝበ ክርስቲያናችንን በመንፈሳዊ ስብከት በዚያን ግዜ ጅምሮ አገልግለው ። ፍሬው ያማረ ከብዙሺህ የሚቆጠር ምእመንን ለንስሐና ለቅዱስ ቁርባን አብቅተዋል፣ ክርስቶስን እንዲያውቁ አርገዋል ፣ሕዝቡ የቤተክርስቲያን ሀብት እንዲሆን አርገዋል።
    A.3/ ሌላው ልነግርህ የምፈልገው ነገር አንተ አቡነ ጎርጎሪዩስን ሳታውቃቸው በፊት ከብዙ አመታት በፊት መምህር ግርማ የአቡነ ጎርጎሪዩስ በፍቅር ተወዳጅ ተማሪ እንደነበሩ እወቅ። በጣም የሚዋደዱ አባትና ልጅ እንደነበሩ ለእውቀት ያህል እንድትረዳ እፈልጋለሁ። ማለት ምኑንም ሳትጀምሩት መምህር ግርማ የመንፈሳዊ ትምህርትና የጸሎት ብርታ እንደነበራቸው ከአቡነ ጎርጎሪዩስ ጋር የጠነከረ የጠራ የአባትና ልጅ የፍቅር እንደነበራቸው ተረዳ።

    ተቺና፣ነቃፊ ስላልሆኑ፣ተንኮል ስለሌላቸው፣በድብቅ ሌላውን ለመጉዳት የማይጠነስሱ ስለሆነ እሳቸው ፍቅር ስላላቸው በጎነታቸውን ስላየ መንፈሳዊ ጉዛቸውን ክርስቶስ ስለወደደው እሱ አብዝቶ ሰጣቸው
    እርግጠኛ ነኝ ይህ ሁሉ አልታየህም ያየህው በምን አይን እንደሆነ አልገባኝም

    B/ የጸሎት ሕይወት ላልከው መንፈስህ ከፈቀደልህ ጠጋ ብለህ ጠይቃቸው እያቸው ። እግዚአብሔር እረድቶአቸው ምን ያህል በጸሎቱ ህይወት እንደረዳቸው ግንዛቤ ታገኝ ይሆናል
    C/ ሌላው ነገር ወገንህ ምን ያህል በእርኩስ መንፈስ እንደተወጠረ የገባህ አይመስለኝም። መሰበኩን ብዙ ትናገራለህ እንጂ የልቡን ጭንቀት ለማየት የተጠጋህ እንካን አልመሰለኝም። አንተ እንዳልከው ማጥመቅ ስራው የሆነ የለም ብለሃል ይህ ያንተ አባባል ነው ። እግዚአብሔር ከተያዘውና ካለቀው ትውልድ አንፃር እንዲያገለግሉ ከወደደላቸው አንተ ምን አስቀናህ አገባህ ።
    ክርስቶስ ልጆቹ ይድኑ ዘንድ ፍላጎቱ ነው ። እውነት እልሃለሁ በኔ እይታ ደግሞ አንተ ያልከው የመዳንን በር የሚዘጋ አባባል ነው ፣ ትውልድ በሰይጣን ተጨንቆ ይኑር ብዙ ግልፅ የሆነ ጥምቀትና መናፍስትን ማስወጣት ጥሩ አይደለም ይበቃል የሚል አባባል ያዘለ ይመስላል::

    D/ የመንፈስ ቅዱስን አሰራር ከመረጃ ፍለጋ ልታገኘው አትችልም በፍጹም ልትደርስበት አትችልም ካልተፈቀደልህ
    E/ ላንተ ጥያቄ ... ክርስቶስ ሲመርጣቸውና ሲያድርባቸው ላንተና አልገባ ላላቸው መንገር ነበረበት እንዴ??
    አንተን መጠየቅ ነበረበት ወይ?? ይህን በእውነት ከመለስከው ግራ ሊያጋባ ለፃፍከው ነግር ብዙው መልስ ይሆንሃል

    ቁ2/ A/ ሌላው ነገር ለምሳሌ አንተ ….. ከመምጣትህ በፊት ዳንኤል ክብረት ሊመጣ ነው ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ተብሎ ከወር በላይ አይደል እንዴ ጥሪውና ዝግጅቱ ... ምን አለበት ታዲያ መምህርም በተሰጣቸው ጸጋ የወንጌልና የፈውስ ግልጋሎት ማዘጋጀቱ ምኑጋር ነው ችግሩ? ባይሆን ጥላቻ ካልሆነ
    B/አንድ ነገር ልንገርህ ክብሬ ይገለጣል ብለህ ከምትሸሽ ። ተገልጠህ ነፍሳትን ማዳን ወደ ክርስቶስ ማምጣት እንደሚበልጥ እርግጠኛ ሆኜ እነግርሃለሁ።
    C/ ሌላው ስለሌሎች ክብር መገለጥ መጨነቅህና ስብከትህ በዚያ ዙሪያ ማጥፋትህ ጥሩ አይደለም ። ያአንድ ግለሰብ መምህር ራሳቸውን ጠንቅቀው ከክርስቶስ ጋር ስለሚያውቁ ብዙ አትድከም። በቅድስና ላይ ብታተኩር ይሻላል
    D/ ስለመሸጥ ተናግረሃል .. ልጠይቅህ ጥንት አባቶቻችን መጸሐፍ መሸጥ የሚባል ነገር አልነበረም ። አንተ ወይም ሌሎች ለምን መጸሃፍ ትሸጣላቹሁ? ይህን ከመለስክ መምህር ለምን እንደሚሸጡ መለስክልን ማለት ነው።
    E/ብዙ ነገሮችህ ቅዱሳኖችን እየጠራህ እነሱ እንዲ አያረጉም ነበር እነዚህ ግን እንዲህ ነው ትላለህ ። አሁንም ልጠይቅህ ... የድሮዎቹ ሰባኪ ለአገልግሎታቸው ብር አይቀበሉም ነበር ። ልምንድነው አንተም ሌሎችም ግን የግልጋሎት ዋጋ በብር ይሰጣቹሃል ለምን ይመስልሃል? ... ይህን ከመለስክ መምህር ለምን እንደሚሸጡ መለስክልን ማለት ነው። በተጨማሪ ላሳውቅህ የምፈልገው መምህር ሁሉ ጋር በነፃ በፍቅር ነው የሚያገለግሉት ሰዎች አስገድደው ዋጋ ካልተቀበሉ ብለው ያስገድዳሉ እንጂ

    ቁ3/ በኢየሱስ አልወጣም በማሪያም ነው ብለሃልይህ? እዚህ ጋር እንደመናፍቅነት እይታህ የጎላ ነው ። ይህ በስህተት እይታ ያየ ፣ የሰይጣንን ቃል ሰምተህ እንጂ መምህር ጋር እንዲህ አይደለም ። እይታህ ለመንቀፍ ችኩል እንደሆነ እረዳለሁ።
    አጋንንት በሚካኤል ስም ቢወጣ ። የክርስቶስን ክብር ዝቅ ማረግ አይደለም ።በሚካኤል ስም ቢወጣ የጌታ ፈቃዱ ሆኖ መሆኑን ዘንግተሃል። በየትኛው አይን እና ህሊና እንዳየህው እራስህን ጠይቅ?
    ቁ4/አንተ በመቁጠሪያ ይወጣል ይላሉ ብለሃል:: እይታህ በጣም መሳሳቱን እይ ። እሳቸው እንዲህ አላሉም ከሄዱበት መንፈሳዊ መንገድና ጉዞ አንፃር የተደበቀ መናፍስትን በክርስቶስ ስም ማድከሚያ የእኛ ጦር መሳሪያ ነው። አሁንም ላይገባህ ይችላል ግን ምን ማረግ ይቻላል ለብዙዎች ግን ጦር መሳሪያችን ነው እወቀው።

    ReplyDelete
  2. ቁ5/ያ ግዜና ይህ አንድ አይደለም ለምሳሌ በዚያ ግዜ ከ200 ሰው 1 ስው በመናፍስት የተጎዳ ነበር አሁን ግን ከ200 ሰው በትንሹ 190 ሰው የተጠቃ ነው።
    ሌላው ደግሞ መተተኞቹና አስማተኞቹ በጣም በዝተው ። ትውልዱን ከዲያብሎስ ጋር አንድ ሆነው በስውር የጨረሱበት ዘመን ነው ።ሰይጣንን ለአላማቸው ጠርተው ሂድ ይህን አድርግልኝ የሚሉ ብዙ እንዳሉ እኔ ላንተ አልነግርህም ። አይ አላውቅም ውሸት ነው ካልክ የቆሎ ተማሪ የሆነን ሰው በተወለድክበት ቦታ ጠይቃቸው በጣም ብዙ ይነግሩሃል።
    አንተ እንዳልከው ይህ የሰይጣንን ኃይል የሚያሳይ ነው ብለሃል ። እየውልህ እይታህ በተሳሳተ መንገድ መቆሙን አየን ።የእኛ እይታ ደግሞ ደግሞ የሰይጣን ደካማና አልቃሻ ነቱን በክርስቶስ እንዴት እንደሚባረር ተረዳን መምህር ግርማ አስተማሩን ።
    ይህ ሁሉ ሰው በሰይጣን ሲያዝ ክርስቶስ የለምን ጥምቀቱና ቁርባኑ አይሰራምን ብለህ ጠይቀሃል
    ጥያቄ ላንተና የተመሳሰለ ሃሳብ ላላቸው
    በመፃህፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙዎች ተይዘው የተጎዱ አሉ ። ለምን ይመስልሃል ሲያዙ ዝም የተባለው? ይህን ከመለስክ አሁንም መልሱን አግኝተሃል።
    ክርስቶስ ነፃነት ሰጥቶናል ግን በራሱ እጅ ሰው ይያዛል። ጥምቀቱና ቅዱስ ቁርባል ታላቅ የክርስቶስ ልጅነትና ኃይልን አሲዞን ነበር ነገር ግን በራስ እጅ የዲያብሎስ እጅ ውስጥ እየገባን እንጂ
    ቁ6/ክፉ የሚሰሩ ሰዎች ይጋለጡ ዘንድ ለነሱና ለዲያብሎስ አጋዝ የሆነ አስተያየት መሆኑን እገነዘባለሁ። ሰይጣን ውሸታም ነው ። የክፉዎች መረብ የመታቾች ተንኮል የነቃና ይፈርስ ዘንድ የማይፈቅድ ጥንቃቄ ያለበት አባባል ይመስላል
    ቁ7/መምህር ግርማ ይህ ቅድስና ነው አላሉም ። ለክርስቶስ መንጋ እንዲያገለግሉ ክርስቶስ ሾማቸው እንጂ። በክርስቶስ ሹመት አንተ ምንም አያገባህም ። ብትችል ከበረከታቸው ተካፈል እንጂ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ልትል አቅሙም ስልጣኑም የለህም ። ገዳምም ይሁን ከተማ በክርስቶስ ምርጫና አሰራር የሚያገባህ አይመስለኝም።
    ቁ8/አንተ የወደፊቱን አሳች እያሰብክ እየፈራህ ዛሬ ክርስቶስ የመረጣቸው የጠራቸውን መምህር ግርማን ወቃሽና አዋራጅ ለመሆን ምክንያት ትደረድራለህ ። ከሩቅ ሆነህ መረጃ ሰብስበህ ያወሩልህን እውነት ብለህ ከምትነዛ ቀረብ ብለህ ትምህርታቸውን ተማር በጣም ብዙ ትምህርት ታገኝበትና እይታህ ይቃናል የክርስቶስ ሐዋሪያ መሆናቸውን ትረዳለህ። ለዚህ እድል ክርስቶስ ይርዳህ።
    ቁ10/ ከክርስቶስ ይልቅ መምህር ግርማ አልጎሉል አልከበሩም ይህ እይታህ እዚህ ጋር እንደመናፍቅነት እይታህ የጎላ ነው ። በመምህር ግርማ ስብከትና ፈውስ ክርስቶስ ከበረ ክርስቶስ ሰራ እንጂ እኔ ያሉበት ቦታ አላየሁም ።ሌሎች ሌላ ነገር ብለውክ ይሆናል በራስህ ቀርበህ ከማየት ይልቅ።
    በአጠቃላይ በመምህር ግርማ ዙሪያ ላወጣህው ድብቅ ገላጭ ጽሁፍ ወንድማችን እይታህ እንደተሳሳተ እነግርሃለሁ ሕዝቡም አይቶት ይመሰክራል
    ሁሉ ሰው እንደ እምነቱና እንደገባው መጠን መርከስም መቀደስም ተፈቅዳል ስለዚህ መቀበልም አለመቀበልም እንደዚሁ ። እኔ ለምን መምህር ግርማን አልተቀበላቹሁም አይደለም ነገር ግን
    ልክ ለሌላው ሊድን ሲል ከሰይጣን ሰንሰለት ሊላቀቅ ሲል ግን ብዙዎች አወቅንልህ ብለው የሚከለክል የዲያብሎስን ያህል ምክር ይመክራሉ ... ሰውየው ግን ተይዞ ለዘመናት ሲያነደው ማንም ትንፍሽ ያላለ .... የመዳኛው ሰአት ሲደርስ ግን ... ሁሉ የሞት ሽረት ላንተ ጠበቃ ሆኖ ሲከለክልህ ግራ ሲያጋባህ ይታያል ። ይህም ያስጠይቅሀል....
    “ሉቃ 11፥52
    እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ”
    የሌላውን ሰይጣን ያሰረበትን ሰንሰለት እንዳይበጠስ ወደ መዳን የሚገቡትን ከልካይ ሆነህ መቀመጥህን አስተውል
    አስተውል ልኡል እግዚአብሔርን ዝም ብለህ ተቃዋሚ ሆነህ መቆምህን እንድትረዳ ልብህን መርምረው። አንተ ክፍ ትውልድ ልኡል እግዚአብሔር ያነሳውን ባለሞል ልታሰናክል እንደማትችል እነግርሀለሁ ።ባይሆን በምኞትህ እንደምትወድቅ የጌታ መለኮታዊ ቃሉ ይነግረናል:: ከመደፋፈርህ በፊት አስተውል ከቻልክ ቅዱስ መንፈስ ካለብህ በፀሎት ጌታን ለምን!!
    እግዚአብሔር መምህር ግርማን ሀይሉን ፍቅሩን ለመንጋው የገለጠባቸው የሚገልጥባቸው ታማኝ ባለሟል ከሆኑት ውስጥ ስለሆኑ ።(ይህንንም ስል በሌሎች በጣም ብዙ አባቶቻችን ገልፃል ይገልፃልም ማለቴም ነው)እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሳቸው በኩል ስለሚገስፀን የጌታን ቃል እንማራለን እናድጋለን ። ግን ሌሎች በቅናት ልቦና ቆመው ሆይ ሆይ እንደሚሉት “አድናቂና ዝምብሎ ተከታይ ቲፎዞ ግን አይደለንም”

    መንፈሳዊ ወገኖቼ አምላካችን ክርስቶስ በባለሞሉ በመምህር ግርማ በኩል ሊያሳስበን የፈለገውን መንፈሳዊ ንቃት ያስተዋላቹሁ ። አይዛቹሁ በርቱ አብዝቶ ይግለፅልን በሀይማኖት ምግባር ፍቅር እምነት በርቱ ”ፊሊጽሲዮስ 1፥ 28-29 በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ” ሳያውቁ ግራ ለተጋቡብን ወገኖቻችንም በፀሎታቹሁ አሳስቡላቸው ወደማስተዋል ህሊና እንዲኖሩ

    በወደደን በክርስቶስ እንሻገራለን!!

    በክፍል ሁለት እንገናኝ!

    ReplyDelete