(በ፰/፲/፳፻፮
ዓ/ም [15/6/2014 EC] በጣሊያን ሮማ
ከተማ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፥ የደብረ ከነዓን ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ቅጽር
ግቢ ካነሳዋቸው ፎቶዎች።)
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛው መልእክት በምዕራፍ አንድ ቁጥር አስራ ዘጠኝ ላይ እንዲህ ይላል፦ "ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።" /፩ኛ ዮሐ ፭፥፲፱/
አምላካችንና መድኃኒታችን፣ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዚህ ዓለም ላይ በነበረበት በሥጋ ወራት፤ "የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ" /፩ኛ ዮሐ ፫፥፱/ ይህ የተገለጠው፥ አምላክና መድኃኒት ነው። አልፋና ኦሜጋ ነው፣ አልፋና ዖሜጋ፥
ፊተኛውና ኋለኛው ነው፣ መጀመሪያውና መጨረሻው እርሱ ነው፤ እኔ ነኝም ይላል። /ራእ ፳፪፥፳፫/ እርሱ ከዳዊት ዘር የተወለደው፦
የእግዚአብሔር ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ፣ አማኑኤል የተባለው፤ እርሱ መድኃኒትና ፈዋሽ፤ ለዓለም የተሰዋ በግ ነው።
ይኼ ሥም፥ አጋንት የሚንቀጠቀጡበት፣ ኃያላን በረዓድ የሚርበተበቱበት፣ ነገሥታት
ጉልበታቸውን የሚያንበረከኩለት፣ ጥበበኞች መዕባ የሚያቀርቡለት፣ ምላስ ሁሉ የሚያመሰግነው፣ ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣
የዘለዓለም አባት፣ የሠላም አለቃ፣ አማኑኤል፣ ኤልሻዳይ፣ አዶናይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
"ስለዚህ፥ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ" /፩ኛ ዮሐ ፫፥፱/ ለሠው ልጅ ጠላት የኾነው ርኩስ መንፈስ ቀርቦ፦ "ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው።" ብሎ፤ ዲያብሎስ፥ ራሱን የስልጣን ባለቤት እንደኾነ በመቁጠር፤ ከአምላካችንና ከጌታችን ጋር ስለ ዓለማት ነገሥታት ክብርና ዝና፣ ላልተገባ የክፉ ስግደት እንዲሰግድለት በጠየቀው ጊዜ አምላካችን ክርስቶስ "ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል" /ሉቃ ፬፥፩-፲፫/ ብሎት፤ የዲብሎስን የተንኮል ሥራ እንዳፈረሰ፣ ርኩስ መንፈስ እንደገሰጸና ለመንፈሳዊ አባቶች ስልጣንን፣ ለእኛ ለምዕመናን አማኝ ደግሞ እንዴት መጽናት እንዳለብን የነፍሳችን መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል፣ በምግባር፤ አስተምሮናል።