Friday, December 28, 2012

በተሰደብክ ጊዜ


      ስለዚህ ወዳጄ፦ እንደ ቃየን ላለመሆን እንደ እንደ ንጉሱ ዳዊት ለመሆን በተሰደብክ ጊዜ፣ በውይይቶች መሐል፣ በባልና በሚስት፣ በቤተሰብ፣ በመስሪያ ቤት፣ በት/ቤት፤ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ይህን በመሳሰለው ባለመግባባት ችግር ጊዜ ይሄን አስታውስ!። እግዚአብሔር፦ ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ በል። በዚህ ጊዜ ሞኝነትን ሳይሆን ገንዘብ ያደረከው ትዕግስትንና ታጋሽነት ነው!  
             ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር። ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎችም ድንጋይ ይወረውር ነበር በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ። ሳሚም ሲረግም። ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ ይል ነበር። ንጉሡም ዳዊትም እንዲህ አለ። እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ። ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው። ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር። ንጉሡና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ሁሉ ደክመው ነበር፥ በዚያም ዐረፉ። / 2 ሳሙ 16/ 

        ወዳጆቼ አያቹ፦ ንጉሡ ዳዊት ኃያልና ብርቱ በነበረ ጊዜ ማንም አልተናገረውም ነበር።  ወዳጄ የምትሰደበው ስድብ በየታኛው ጊዜና ሠዓት እንደሆነ ልብ ብለህ ከላይ ከገለጥኩልህ ከንጉሡ ዳዊት ጋር ራስህን ነጻፅረህ መርምር። ሃብታም በሆንክበት ጊዜና አንቱ በተባለክበት ወቅት እንደማይሆን አስብ፥ ይልቁንስ ስድብ የሚበረታብህ ነገሮች ውስብስብ ባሉብህ ወቅቶች መሆኑን ተረዳ። ለዚህም ነበር ንጉሡ ዳዊት ከልጁ ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜና ከደብረ ዘይት ዐቀበት ወደ ተራራው አካባቢ ያልጠበቀው ሰው ሳሚ የሚባል ያጋጠመው፥ ሳሚም ድንጋይ እየወረወረበት፣ አፈርና ትቢያም እየበተነበት፤ እየሰደበውና እየረገመው ንጉሡ ዳዊት ሰምቶ እንዲህ አለ፦ ተውት ያሻው ይበል ነበረ ያለው። እንደውም ስድቡንና እርግማኑን ከእግዚአብሔር እንደ ታዘዘ ነበር የተመለከተው። 

        ወዳጆቼ፦ እኛስ ስንሰደብ ስንቶቻችን ይሆን አጸፋዊ ስድቦች የምንመልሰው በዚያ ላይ ከስድቡ በላይ ለመማታትና ለመደባደብ፣ ይባስም ካለ ደም እስከ ማፍስና እስከ መግደል ይደረሳል፤ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ እሩቅ መሄድ አያስፈልግም። በአገራችን በተለያዩ የህዝብ ሚዲያዎች፦ እንደምንሰማው ከቀላል ንግግር ወደ ስድብ፣ ከስድብ ወደ አጸፋዊ መልስ፤ ከአጸፋዊ መልስ ወደ ዱላ ማንሳትና መማታት ወደ  መማታት ስሜታዊነት ውስጥ ሲገቡ ደግሞ ወደ ማይወጡብት ታላቅ የሆነ ኃጢአትና ልሸከማት የማልችላት የህሊና ፀፀትና ሰቀቀን ሁልጊዜ እየተብከነከንን ያቺ ዕለትና ቀን እያልን ዕድሜያችንን ስንረግምና መፈጠራችንን ሁሌ እየረግምን በምድርም ላይ እንሆን ወ መጥምግ እንገልን። ይሄን ጊዜ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እንሆናለን፥ የሚያገኘንም ሁሉ የደመኛዬ ሰዎች ናቸው በማለት ሕይወታችን በፍርሐት ሰላምና ፍቅር ናፋቂ ከመሆን ውጭ፤ የሰላምና ፍቅር ተካፋይ ወይም ተሳታፊ (ሱታፌ) ሳንሆን ናፋቂ ብቻ ሆነን እንቀራለን።

        ደግሞም ምን ይሄ ብቻ በዚህ ዓለም በፍትህ ፍርድ ውስጥ (በእስር ቤት) በእግዚአብሔር ፊት ደግሞ ልንወጣው የማንችለው ኃጢአት እንሸከማለን። ቃየን እራሱ "ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት" ሲል መስከሯል። ታዲያ ይህ ሁሉ የኃጢአት፣ የህሊና ፀፀት፣ የመሳቀቅ፡ የመብከንከና የፍርድ፤ ውጤቱ ከየት ተገኘች፣ ከየት መጣች ቢሉ፥ ስድብን ያለመታገስና እንደው ለምን ተስደብኩኝ፣ ለምን ተነካሁኝ የሚለውን የስድቡ ፍሬ ሆኖ እናገኘዋለን። 

       መሰደብ ወደ አጸፋዊ ስድብ ሊወስደን ይችል ይሆናል አልፎም ወደ ስሜታዊነት ያስገባንና ልንወጣው የማንችለው አዘቀት ውስጥ ይከተናል ቢሆንም ግን ከዚህ ሁሉ አዘቀት ሊከተን ወደ ሚቸለው ጸያፋዊ ስድብ ከምንለዋወጥ ይልቅ እግዚአብሔር ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ (ይስደበኝ) ብለህ ነገሮች አሳልፍ። ሰምተህ እንዳልሰማህ፣ አይተህ እንዳላየህ ሁን። ምናልባት በዚህ ቀን (በተሰደብኸ ቀን) መከራህን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልሃል።

       እውነቴን ነው የምልህ መልካም ባይመልስህ እንኳን ጥልን በምድር ላይ ታበርዳለህ፣ ትዕግስትን፣ ታጋሽነትን፣ ልበ ሰፊ ነገር አላፊ፤ መሆን በሕይወት ላይ በተለማመድክና ይህን ባደረክ ጊዜ ለሰዎች ምሳሌና አርዓያ ትሆናለህ። የሰደበህና የረገመህ ሰው እንኳን አንደበቱን ከፍቶ በአፉ ባያመስግንህም እንኳን ስለ ታጋሽነትህና ስለ ትዕግስትህ እያየ በልቦናው እንዴት ያለ ሰው ነው! እያለ በመገረምና በመደነቅ ያመሰገንህ።

No comments:

Post a Comment