Saturday, January 5, 2013

ከንብ፣ ከውሻ፣ ከእባብ ምን እንማር?

            እውነት ነው፥ አብዛኞቻችን እነዚህ ስሞች ስንሰማ ከፊታች የሚታየንና በህሊናችን የምናስባቸው፣ የምናሰላስለው ጎጂ መሆናቸው ነው። ለመሆኑ በበጎ ጎን እይታ ስንቶቻችን ተመልክተናቸው። ማጋነን ባይሆንብኝም በተቃራኒ እይታ ነው አብዛኞቻችን የምንመለከታቸው። ለዚህም ነው ከንብ፣ ከውሻ፣ ከእባብ ምን እንማር?” ብዬ እርስ የሰጠሁት። ንብን የምናውቃት በተናዳፊነቷ ነው፣ ውሻን ደግሞ በተናካሽና በአስደንጋጭነቱ ነው፤ እንዲሁም ደግሞ እባብን መርዘኛና ገዳይ እንደሆነ ነው። እንግዲያውስ ከተለያዩ ጸሐፊያንና መምህራን ያነበብኳቸውንና የሰማሁትን እነሆ ለእናንተ ለወዳጆቼ አብረን በጎ በጎ ጎናቸውን እናነበው ዘንድ አቀረበኩ። መልካም ምንባብ!


                          1. ንብ፦
            ወለተ ጴጥሮስም እንዲህ አለቻቸው ‹‹ንብ ታውቃላችሁ? ንብ መልከ ጥፉና ክፉ ናት፡፡ መርዟም ሰው ከነደፈ ይጎዳል፡፡ ያምማል፡፡ አንዳንዴም ለመሞት ያደርሳል፡፡ ማንም የንብን ጠባይ አይወደውም፡፡ ከንብ ይልቅ ዝንብ ጠባይዋ መልካም ነው፡፡ አትናደፍም፤ መርዝ የላትም፤ አትጎዳም፤ በመርዟም ለሞት አታደርስም፡፡ ዝንብን የንብ ያህል ማንም አይፈራትም፡፡ ግን ዝንብ ማር አትሠራም፡፡ ለዝንብ ማንም ቀፎ አይሠራላትም፡፡ ምክንያቱም ማር የላትምና፡፡ ሰው ሁሉ የንብን ጠባይዋን ታግሦ፣ መርዟንም ተከላክሎ ለማርዋ ሲል አብሯት ይኖራል፡፡ ማንም ስለ ንብ ክፋትን መርዝ አያስብም፤ ስለ ማርዋ ነው እንጂ፡፡
        ‹‹እኔም እንደዚያው ነው፡፡ ይህች ባልቴት ጠባይዋ ክፉ ነው፡፡ ነገር ግን ከእርስዋ ዘንድ እንደ ማር የሚገኝ ብዙ በረከት አለ፡፡ ንብ ሌላውን የምትጠቅመውን ያህል ለራስዋ አትጠቀምም፤ ይህችም ሴት እኔን የጠቀመችኝን ያህል ራስዋን አልጠቀመችም፡፡ እዚያ ቤት ብዙ ነገር አጋኝቻለሁ፡፡ ጠባይዋን ታግሼ፣ መርዝዋንም ተከላክዬ ብዙ ማር ቆርጫለሁ፡፡ እናንተ መናደፏንና መርዟን ብቻ ነው የምታዩት፡፡ ማርዋ ሊታያችሁ አልቻለም፡፡ እኔ ደግሞ ማሩ እንጂ መናደፏ አልታየኝም፡፡›› አለቻቸው፡፡

                             2. ውሻ፦
 
         ልቅማን የተባለ ፈላስፋ ስድስቱን ነገሮች ገንዘብ ያደረገ ሰው ፍጹም ነው ፍጹም ይሆናል ብሏል።  የፋርስ (ፔርሲያ) ሰዎች እነዚህን ስድስቱን ነገሮች በውሻ ይገኛሉ ይላሉ። እነሱም፦ ስምምነት፣ ፍቅር፣ ልቦና፣ ትዕግስት፣ ማመስገን፤ ተስፋ ናቸው።

1. ተሰናዕዎ (መስማማት)፦ ውሻ፥ ይንቁታል ያባርሩታል። ነገር ግን ከጌታው ቤተሰብ ጋር ስለ ተስማማ ከጌታው ቤት አይወጣም። መስማማት ማለት ይህ ነው።

2. ፍቅር፦ ውሻ፥ ቢያበሳጩት፣ ቢደበድቡት፣ ቢያስርቡት፣ ቢያስጠሙት፤ የጌታውን ቤተሰብ ስለ ወደዳቸው ከፋኝ፣ መረረኝ፤ በሎ የጌታውን ቤት አይለቅም። ፍቅር ማለት ይህ ነው።

3. ልቦና፦ ውሻ፥ ቢቆጡት ቁጣውን ታግሶ ዝም ይላል። ያዘዙትን ሁሉ ያደርጋል፥ ማለት ውጣ ቢሉት ይወጣል፣ ና ቢሉት ይመጣል፣ ያዝ ቢሉት ይይዛል፣ ልቀቅ ቢሉት ይለቃል፤ ልቦና ወይም ማስተዋል ማለት ይህ ነው።

4. ትዕግስት፦ ውሻ፥ ስለ ጌታው ቤት ከሌባ፣ ከአውሬ፤ ከማንኛውም ጠላት ይታገላል። ስለ ጌታው ሕይወቱን አሳልፎ ይሰጣል። የመጣበትን ፈተና ችሎ በኃይል የሚበልጡትንና የሚበረቱበትን ያባርራቸዋል፤ ትዕግስት ማለት ይህ ነው።

5. አዕኵቶ (ማመስገን)፦ ውሻ፥ ረኃቡንና ጥሙን ታግሶ ይቀበለዋል እንጂ ለማንም እስራቡኝ አስጠሙኝ ብሎ ጌታውን አያሳጣም፤ አያማርርም። ማመስገን ማለት ይህ ነው።

6. ተስፋ፦ ውሻ፥ ይሰጡኛል በማለት ተስፋ አድርጎ፣ ከጌቶቹ ፊት ሁል-ጊዜ በመሽቆጥቆጥ ይለማመጣል፤ ጅራቱን ይቆላል። ተስፋ ማለት ይህ ነው።

እነዚህ ስድስቱን የበጎነት ጠባዮች (ግእዛን በሌው ውሻ) ሲገኙ፥ ግእዛን ያለው ሰው፣ እነዚህን ጠባዮች ሳይኖሩት ቢገኝ ከውሻ ያነሰ መሆኑን ገምተው ይንቁታል፤ ያቃልሉታ።

                                3. እባብ፦

         እንደ እባብ ልባም እንደ እርግብ የዋህ ሁኑ። ይህቺን አስቸጋሪ ዓለም ድል ለማድረግ፣ ፈተናውን ተወጥታቹ ለክብር ለመበቃት፣ እባብ ሁኑ፤ እርግብ ሁኑ። ምናልባት እንደ እባብ ልባም እንደ እርግብ የዋህ የሚለውን ቃል ስንሰማ የምናስበው ብዙ ነገር ሊኖር ይችላል በውስጣችን። ለምሳሌ፦ እባብን የምናውቀው በተናዳፊነቱ ነው፥ እባብ ሲባል ተናዳፊ፤ መርዘኛ ነው። ታዲያ ጌታችን እንደ እባብ ልባም ሁኑ ማለቱ ሰውን ተናደፉ ይሆን? ሰውን ሁሉ ፈጁት ነውን? አይደለም!።

እንደ እባብ ልባም ሁኑ ሲል ምስጢር አለው ትርጉም አለው። እባብ ልባም ነው አስተዋይ ነው። አስተዋይ ሁኑ እንደሱ፥ በማስተዋል ኑሩ ሲል ነው። አንዳንዴ ከጠላትም በጎ ጎን ይወሰዳል። ከእባብም በጎ ጎን የምንወስደው አለ፥ ተናዳፊነቱን ሳይሆን፣ ክፉነቱን ሳይሆን፤ በጎ ጎኑን አስተዋይነቱን እንወስዳለን።

        እባብ ከእዚ ተነስቶ እዛ ለመድረስ እስተውሎ ነው የሚጓዘው፥ ድንገት ተነስቶ አይሮጥም። አንዳንድ ሰው በጣም ብልጥ ሲሆን፣ አስተዋይ  ሲሆን፤ ይህ ሰው እባብ ነው ይባላል። እንደውም እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ ይባላል። በጣም አስተዋይዎች ከሆኑ በልጥ ለብልጥ ከሆኑ ሁለት ሰዎች ይተያያል ካብ ለካብ እሱ እባብ ነው ይባላል። በማስተዋል ነው የሚኖረው፥ እድሜው እረጅም ነው። እያንዳንዱን ነገር አስተውሎ ስለሚሰራ ከጥፋት እራሱን እየጠበቀ ነው የሚኖረው እባብ። ለዚህ ነው እንደ እባብ ልባም ሁኑ የተባለው።

የእባብ ልባምነት አባቶቻችን ጥሩ አድርገው ተርጉመውታል። ከልባምነቱ መካከል አንዱን እናያለን።

         ለምሳሌ አንዱ የእባብ ልባምነት፦ እባብ እፀ ዘይ የሚባል እፅ አለች፥ ዛፍ ላይ ያለች እፅ አለች። በጣም እሱ የሚበላት፣ የሚወዳት እፀ፤ እፀ ዘይ ትባላለች። ይህቺ እፅ ሊበላት ሲሄድ፥ ይወዳታል ብለናል፣ አንድ ችግር አለባት፤ ፈተና ትፈጥርበታለች። እፁ እዛ ዛፍ ላይ ያለው ፍሬው ይስማማዋል፤ ግን እባብ ምንድን ነው የሚሰራው ወደዛች ፍሬ ሁልጊዜ በሄደ ቁጥር፥ ፍሬዋ ያለችበት ዛፍ ጥላ ካረፈበት ግን ጥላው ያደክመዋል። አስተውሉ ፍሬው ይስማማዋል ጥላው ግን ያደክመዋል፣ ያፈዘዋል፤ ሰው ያገኘዋለል እዛው ፈዞ እንደወደቀ። ይህን ያውቃል እባብ ፍሬው እንደሚስማማው፣ ጥላው እንደሚያደክመው፤ ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህ በሬ ሆይ ሳሩን ሳሩን ስታይ ገደሉን አላየህ አይደለም አካሄዱ። እንደሮጡ አይገባበትም።

         መጀመርያ በሩቅ ዛፉ ጋር ከመድረሱ በፊት አሻቅቦ ፍሬውን ይመለከትና የዛፉ ጥላ በየት በኩል እንዳለ ያያል። የዛፉ ጥላ በስተ ግራ ከሆነ እሱ ቀስ ብሎ ጥላው ሳያገኘው፥ የሚያደክመውን ጥላ ሽሽት ነው ጥላው ሳያገኘው ቀኝ ቀኙን ወጥቶ ዛፉ ላይ ፍሬውን በልቶ ተመልሶ ወርዶ ይሄዳል። የዛፉ ጥላ በስተ ቀኝ ከሆነ ጥላውን ያውቃል፥ ፀሐይ ፀሐዩን ነው እሱ የሚሄደው። በብርሃኑ በኩል ወጥቶ ጥላው ሳያገኘው ፍሬውን ቀጥፎ በልቶ ይሄዳል። እንዲህ አስተዋይ ነው! በጥበብ የሚመገበውን ነገር ይመገባል። እናንተም እንደ እባብ፥ ዛፍ፦ የተባለች ይህቺ ዓለም ናት። ከዚቺ ዓለም የምንበላ ፍሬ አለ (ይትቃወመ ነፍስ ዘ እንበለ ስጋ) ነፍስ ያለስጋ አትቆምም። የግድ ሰርተን፣ ወጥተን፣ ወርደን፣ ደክመን፤ ከዚህ ዓለም የምንወስደው ፍሬ አለ። ግን የዚህን ዓለም ፍሬ ለመመገብ ስትፈልጉ፥ ጥላዋም እንዳትጥልባችሁም እየተጠነቀቃቹ፣ እባብ ፀሐይ ፀሐዩን ወጥቶ ፍሬ እንደሚበላ፤ እናንተም ፀሐይ ፀሐዩን ውጡ።

        ፀሐይ፦ የተባለ ህጉ ነው፥ የእግዚአብሔር ህግ ነው። የእግዚአብሔር ህግ የተባለ ብርሃን ነው፤ ወንጌል ነው። በወንጌል በኩል፣ በብርሃኑ በኩል፤ የአለምን ፍሬ ተመገቡ። እንደ ህጉ እየተዛጓቹ፣ ንስሐ ገብታቹ፣ ስጋ ወ ደሙ ተቀብላቹ፣ ሳትሰርቁ፣ ሳታታልሉ፣ በሚዛን ሳትበድሉ ሰውን፤ በብርሃን እየተጓዛቹ፥ እግዚአብሔር በማያዝንበት መንገድ እየተጓዛቹ የዚህን ዓለም ፍሬ ብሉ። እንጂ፥ በጥላ ከሔዳቹ ጥላ የተባለ ጨለማ የተባለ ህግ መጣስ ነው፣ ኃጢያት ነው፣ በደል ነው። ሰው ፍሬ እበላለሁ ብሎ ለስጋው የሚሆን ነገር አገኛለው በሎ በሚዛን ከበደለ፣ ካታለለ፣ ጉቦ ከበላ፣ ዳኛም ከሆነ አድልቶ ከፈረደ፤ በጥላው በኩል ሔዷል ማለት ነው። እንዲህ በጥላው በኩል አትሒዱ በብርሃን በኩል እየተመላለሳቹ የሚያስፈልጋችሁን እግዜር ይሰጣችዋል ተመገቡ ሲለን ነው።

        በብርሃኑ ተጓዙ ዓለም ጥላዋን እንዳትጥልባቹ ተጠንቀቁ “እንደ እባብ ልባም ሁኑ” ያለው ለዚህ ነው። እግዚአብሔር በቸርነቱ፥ በብርሃን ተጉዘን የሚያስፈልገን ነገር እርሱ በቸርነቱ ይርዳን!። አሜን!

ዋቢ
1. ንብ፦ (የምታይበት መንገድ) ከዲ/ዳንኤል ክብረት /ድረ ገጽ/ 
2. ውሻ፦ (መፅሐፈ አንገረ ፈላስፋ ገጽ 170) ከሊቀ መዘምራን ዕቁበ ጊዮርጊስ።
3. እባብ፦እንደ እርግብ የዋሆች እንደ እባብ ልባሞች ሁኑከቀሲስ ያሬድ /መድኅን ከቃለ ወንጌል ትምህርት      
     [ከድምፅ ወደ ጹሑፍ ቀንጭቤ  አቀረብኩት]



2 comments: