Tuesday, January 8, 2013

ተግሳፅ፣ ምክርና ትዕዛዝ፦ (ክፍል ሁለት)

               ፈላስፋው ህርቃን፦ ያዘዘው ትዕዛዝ የመከረው ምክር ይህ ነው
ልጄ ሆይ፦ እግዚአብሔር ባደለህና በወሰነልህ ሀብት አመስግነህ ኑር። እርሱ  እግዚአብሔር ከሰጠህ ሌላ ምን ምን የሚጨምሩልህ የለምና ተስፋህንና እምነትህን በአገልጋዮችህ ላይ አታድርግ።

ልጄ ሆይ፦ የማትወደውንና የማይወድህን ሰው ከማእድህ አታግባ። በማናኛቸውም ነገር ከማይወድህ ሰው ጋር አባሪ አትሁን። ከሁሉ ጋር መቀመጥን አትውደድ።

ልጄ ሆይ፦ ጠላትህ ወድቆ ብታገኘው አትዘብትበት እርሱም በተነሳ ጊዜ በፋንታው እንዳይዘብትብህ ጠላትህ መልካም ነገር አግኝቶ። ደስ ሲለውም ለምን አገኘ ብለህ አትዘን (አትቅና) ክፉ ነገር ሲያገኘውም ደስ አይበልህ (በጎም ሆነ ክፉ ለሁሉ ነውና)።

“ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል፤ ኀጥኣን ግን በክፉ ላይ ይወድቃሉ። ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥ እግዚአብሔር ያንን አይቶ በዓይኑ ክፉ እንዳይሆን፥ ቍጣውንም ከእርሱ እንዳይመልስ።” /ምሳ 24፥16-18/
ልጄ ሆይ፦ ጠላትህ በክፉ (በተንኮል) ቢመጣብህ አንተ በበጎነት (በቅንነት) ተቀበለው ልጄ። 

“ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” /ሮሜ 12፥20-21/     


ልጄ ሆይ፦ ከጯሂና ከተነዛናዥ ሴት ዘንድ አትቅረብ፣ የሴት ተወዳጅነቷ ጠባይዋ፣ ደግ አነጋገርዋ ልዝብ ሲሆን ነው፤ የሴት መውደድዋ ባሏን ደስ ያሰኝዋል።

 የሴት መወደዷ ባሏን ደስ ያሰኝዋል። ጥበቧም ሰውነቱን ደስ ያሰኘዋል።” /ሲራ 26፥14-15/

 ልጄ ሆይ፦ በዕድሜ በማዕረግና በሀብት የሚበልጥህ ቢመጣ ብድግ ብለህ (አክብረው) ተቀበለው። እንዲሁም በዕድሜ በማዕረግና በሃብት ካንተ ለሚያንስ እንዲሁ አድርግ።

ልጄ ሆይ፦ ክፉ ሰው ይወድቃል ከወደቀም በኋላ አይነሳም። ደግ ሰውም ይወድቃል ነገር ግን ቢወድቅ ይነሳል ተመልሶ ከነበረበት ቦታ ይቀመጣል።

“ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል።” (ጻድቅ ሰው ሰባት ጊዜ በኃጢአት ይሰነካከላል ሰባት ጊዜም በንስሐ ይነሣል።) /ምሳ 24፥16/

ልጄ ሆይ፦ ልጅህን ከመስራትና ከመቅጣት ዝም አትበል (ቸል አትበል)። ፍግ ለእርሻ እንደሚጠቅመውና እንደሚያሳምረው እንዲሁም መስራትና መቅጣት ለልጅ ይጠቅማል ያሳምረዋል (ልዝብ ያደርገዋል) የከብት መንጋዎች በመልካም መስክ ተሰማርተው ሲታዩ ደስ እንደሚያሰኙ ሁሉ ተሰርቶና ተቀጥቶ ያደገ ልጅም ያየውን ሁሉ ያስደስተዋል። (አሳዳጊህ ይባረክ እያሰኘ ወላጆቹን ያስመርቃል።)

ልጄ ሆይ፦ ልጅህን ገና ሕፃን ሳለ ይዘህ ስራው ቅጣው፥ ከጎረመሰ በኋላ ልስራህ ልቅጣህ ብትለው ስለጎረመሰ ይታበይብሃል  ሊታገልህም ይቃጣልና፣ ከስድነቱና ከክፉ ሥራው ልትመልሰውና ልታርመው አትችልም፤ ኋላም እሱ በሠራው የብልገና ሥራ ሁሉ አንተ ታፍርበታለህ ትዋረድበታለህ።

ልጄ ሆይ፦ ደፋር ተሳዳቢና የሚኮበልል ባርያ አትግዛ፥ ሌባ ሴት ባርያንም አትግዛ። ከገዛህ (አለበለዚያ) ግን የሰበሰብከውን ገንዘብ ሁሉ ያጠፉብሃል።

ልጄ ሆይ፦ ሐሰተኞች ሰዎች ቢምሉ ቢገዝቱ ነገራቸውን በአየር ላይ በሚበሩና ፍለጋቸውን በማይገኝ ወፎች መስልው፥ ለመብረራቸው ፍለጋ እንደሌለው ሐሰተኞች ሰዎች ለሚናገሩትም ነገር ሥር መሰረት የለውምና።

ልጄ ሆይ፦ ጥበብና ዕውቀት ከሌለው ከደንቆሮ ሰው ከመኖር አትውደድ። ሰው በማይሄድበት በረሃም አትሂድ በዚያ ምን እንደሚቆይህ አታውቅምና።

ልጄ ሆይ፦ የዛፍ ጌጡ ሽልማቱ ቅርንጫፎቹና ፍሬው ናቸው። የተራራም ሽልማቱ ዛፎቹ ናቸው እንዲሁም የሰው ሽልማቱ ሚስቱ ልጆቹና ወንድሞቹ (ዘመዶቹ) ናቸው።

ልጄ ሆይ፦ ሚስትና ልጅ የሌለው ሰው በመንገድ ዳር የበቀለች ፍሬ የማይገኝባት መንገደኖች ቅጠሎቿን እየዘነጠፉ ቅርንጫፎቹን እየቆራረጡ የእግራቸው ትቢያ የሚያራግፉባት የበረሃ እንስሶች (እንስሳ ዘ ገዳም) የሚበሏትን ዛፍ ይመስላል።

ልጄ ሆይ፦ አንተ ዓላዋቂ ስትሆን ባልጀራህን በዕውቀት እኔ እበልጥሃለው አትበለው፥ ፍላጎቱን ተከተል ቃሉን ስማ እርሱ ያመነውን እመን እርሱ የወደደውን ውደድ እንጂ።

            .................................................... ይቀጥላል ...................................................

ዋቢ መፅሐፍ:- አንገረ ፈላስፋ (የፈላስፋዎች አነጋገር) በሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ

No comments:

Post a Comment