Sunday, January 27, 2013

“ቁጣንና ሌሎችንም አስመልክቶ የቅዱስ ኤፍሬም ተግሣጽ”


      "አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ" አለህ። ነፍስህም የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት። እናም ከሰው ሁሉ ጋር በፍቅር በመኖር የእግዚአብሔር አርዓያ የሆነችውን ነፍስህን አክብራት። በምትኖርባቸው ዘመኖችህ ሁሉ በተቻለህ መጠን ሰውነትህን ከቁጣ ጠብቅ። ያለበለዚያ አንተን ወደ ሲኦል ታወርድሃለች፤ ጎዳናዎቿም ወደ ገሃነም የሚያመሩ ናቸው። እናም ቁጣን በልብህ አታኑራት መራርነትንም በነፍስህ አታሳድር በነፍሰህ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህምና ነፍስህን መልካም በማድረግ ጠብቃት

 

አንተ በእግዚአብሔር ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል በክርስቶስ ሕማምም ድነኀል፤ አንተ በፈንታህ ለኃጢአት ሥራዎች የሞትክ ትሆን ዘንድ ስለአንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፋበት መታገሡ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሣቸው አርአያ ሊሆንህ ነው መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው በጅራፍ ተገርፎ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለጽድቅ ስትል መከራን እንዳትሰቀቅ ነው

   ስለእውነት አንተ የእርሱ አገልጋይ ባሪያው ከሆንክ ቅዱስ የሆነውን ጌታህን ፍራው ስለእውነት አንተ የእርሱ እውነተኛ ደቀመዝሙር ከሆንክ የመምህርን ፈለግ ተከተል የክርስቶስ ወዳጅ ትባል ዘንድ ባልንጀራህ በአንተ ላይ ቢሳለቅ ታገሠው ከመድኃኒዓለም የተለየህ እንዳትሆን በሰው ላይ ቁጣህን አትግለጥ

አንተ ከምድር የሆንኽ ሸክላና የአመድ ዘመድ፣ እንሰሳዊ በሆነ ግብርም የተወለድኽ ክብርህን ያላወቅህ እንደሆነ ነፍስህን በቃል ሳይሆን በተግባር ከእንስሳት ለይ ፌዘኝነትን የምታፈቅራት ከሆነ፣ ሁለመናህ እንደ ሰይጣን ነው በባልንጀራህ ላይ የምታፌዝ ከሆነ፣ ራስህን የዲያብሎስ አንደበት አድርገሃል በባልንጀራህ ጉድለትና ድክመት ላይ ስም እየሰጠህ የምትሳለቅ፣ በዚህም ደስ መሰኘትን የምትወድ ከሆነ፣ ይህን ትፈጽም ዘንድ ያተጋህ ሰይጣን አይደለም፤ ነገር ግን አንተ የእርሱን ቦታ በጉልበት ነጥቀህ ይዘህበት ነው እንጂ

አንተ ሰው ከዚህ በደል ፈጽመህ ትርቅ ዘንድ እመክርሃለሁ። ይህ በደል ሰውነትህን ፈጽሞ የሚያጠፋ ነውና። በእርጋታና በሰላም ትኖርና የኃጢአተኞች ተባባሪ በመሆን በእነርሱ ላይ ከመጣው ጥፋት ተካፋይ እንዳትሆን ከፈቀድኽ፣ ከፌዘኞች ጋር አትቀመጥ። ሙሉ ስሙ የወዮታ ምንጭ የሆነውን ፌዘኝነትን፣ የንጽሕና ጠር የሆነውን ዋዘኝነትን ጥላ። በአጋጣሚ ስንኳ ፌዝን ብትሰማ በትምህርተ መስቀል ሰውነትህን በማማተብ ልክ እንደ አቦሸማኔ ከዚያ ቦታ ፈጥነህ ሽሽ። የሰይጣን ማደሪያ በሆነ ሰውነት ውስጥ ክርስቶስ ፈጽሞ ሊያድር አይችልም። ግሩም የሆነው የሰይጣን ማደሪያ በባልንጀራው ላይ የሚሳለቅ ሰው ሰውነት ነው። የጠላት ዲያብሎስ ቤተመንግሥቱ የፌዘኛ ሰው ልቡና ነው። ሰይጣንም በዚያ ፌዘኛ ሰው ልቡና ውስጥ አንዳች ተጨማሪ ክፋት ሊጨምር አይፈቅዱም፤ ምክንያቱም ፌዘኝነት በራሱ ሁሉንም ክፋቶች አሟልቶና አካቶ የያዘ ነውና።

ከፌዘኝነት በላይ የኃጢአተኛን ልብ በክፋት የሚሞላ ነገር ከቶ የለም። ፌዘኛ በፌዙ ገብቶትም ይሁን ሳይገባው ሰውቱን ለጥፋት ያደርሳታል። ቁስሉ ፈጽሞ አይጠግም፤ ለስቃዩም ፈውስ የለውም፤ ለሕመሙም መድኃኒት አያገኝም፤ ለሰቆቃውም ፍጻሜ የለውም፤ እንዲህ ያለ ሰው ላይ ለተግሣጽ ምላሴን አንቀሳቅስበት ዘንድ አልነሣም። በእርሱ ላይ የደረሰበት ውርደት ይበቃዋልና ስለድፍረቱ ያገኘው ቅጣት በቂው ነው።

እንዲህ ይነቱን ሰው ከመስማት ጆሮውን የመለሰ ሰው ብፁዕ ነው እንዲህ ዐይነት ሰውን የማያውቅ ሰውም የተባረከ ነው አንተ የጌታ ቤተመቅደስ (ቤተክርስቲያን) የተባልክ ሰው ሆይ ይህን የክፋት እርሾ በሰውነትህ ውስጥ እንዳይጨምርብህ ይህን ከመሰለ ሰው ፈጽመህ ራቅ የሕይወት መንገድ እጅግ ጠባብ ናት፤ የስቃይ ጎዳናዎቿ ግን እጅግ ሰፊዎች ናቸው

ጸሎት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የምታደርስ ቀጭኑዋ ጎዳና ናት ከኃጢአት በመራቅ የሚቀርብ ጸሎት፣ ፍጹም የሆነ ሥራን ይሠራል ጌታ ሆይ ካለ አንተ አዎን ! ካለ አንተ ጸጋ በቀር የሰው የጽድቅ ሥራ እንደምናምን ነው ድካሙም ሁሉ ከንቱ ፍሬ አልባ ነው ካለ አንተ ጸጋ በቀር የእኛ ባሕርይ በራሱ መልካም ሊሆን ተስኖታል

ከቸርነትህ የተነሣ እኛ ከትቢያ የሆንን የአንተ አርዓያን ገንዘባችን አደረግን። በኃጢአት ውስጥ እንዳንጠልቅ ጌታ ሆይ ለፈቃዳችን ኃይልን ስጣት። የአንተን ክብር ሁል ጊዜ ማሰብን ገንዘባችን እናደረግ ዘንድ ማስተዋልን ስጠን። በኑፋቄ እንዳንጠፋ የባሕርይ የሆነውን እውነት በአእምሮአችን ውስጥ ጨምር። አመለካከታችን በከንቱ እዚህም እዚያም እንዳይባክን ማስተዋላችንን በሕግህ ደግፈው። በእኛ ላይ አንዳች ጉዳትን እንዳያመጡ ጌታ ሆይ የሰውነታችንን ሕዋሳቶች በሥርዓት እንዲመላለሱ አድርጋቸው።

ወደ እግዚአብሔር ቅረብ ሰይጣን ከአንተ ይርቃል” የሥጋ ፈቃዶችን ከልቡናህ አውጥተህ ጣላቸው። እንዲህ በማድረግህ ከጠላትህ ፈጥነህ ልታመልጥ ትችላለህ። ኃጢአትንና መተላለፍን እንዲሁም ሰይጣንን ከነአካቴው የጠላህ ከሆነ ፈጽመው ከአንተ ይርቃሉ።

የትኛውንም ኃጢአት በፈጸምኽ ቁጥር በስውር ጣዖትን እያመለክ እንደሆነ እወቅ። መተላለፍንም በወደድክ ቁጥር በነፍስህ አጋንንትን እያገለገልኽ መሆንህን ተረዳ። በወንድምህ ላይ በጠብ በተነሣሣህ ቁጥር ደግሞ ሰይጣን በእርጋታ እንዲቀመጥ እየረዳኸው ነው ፡፡ ባልንጀራህ ላይ በቀናህ ቁጥር ለዲያብሎስ ሰላምን ሰጠኸው።

አጠገብህ ስለሌለው ሰው ድክመት በተናገርክ ቁጥር፣ ሰይጣን ይዘፍንበት ዘንድ ምላስህን በገና አድርገህ እንደሰጠህ ቁጥር ነው። ጥላቻ በልቡናህ ነግሦ ከሆነ የዲያብሎስ እርዳታ እጅግ ታላቅ ይሆናል። ደስ የማያሰኝ ከንቱ የሆነ ንግግርን የምትወድ ከሆነ ለአጋንንት ድግስ እየደገስክላቸው መሆኑን ተረዳ። (ስለዚህም ነው የሥጋ ሥራዎችን መፈጸም ጣዖትን እንደማምለክ ነው መባሉ።

ዋቢ፦ ከዲያቆ ሽመልስ መርጊያ ድረ ገጽ (ስብከት ወተግሣጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ)


1 comment:

  1. betame dess yemile meker new berta wondme
    ke wolete mariyam

    ReplyDelete