Monday, January 14, 2013

ተግሳፅ፣ ምክርና ትዕዛዝ፦ (ክፍል ሦስት)

                ፈላስፋው ህርቃን፦ ያዘዘው ትዕዛዝ የመከረው ምክር ይህ ነው

ልጄ ሆይ፦ ከዐዋቂዎችና ከብልሆች ሰዎች አትራቅ፥ ምንም እንኳን ጥበባቸውን ባትየዝ ቁጥርህ ከእነርሱ ጋር ይሆናልና ሲልኩህም ሁለተኛ ጓደኛን ጨምሩልኝ በማለት አታስቸግራቸው።

ልጄ ሆይ፦ ባልንጀራህን ስትልከው እሺ በእጄ ያለህ እንደሆነ ባልንጀራው እንጂ ጌታው አለመሆንህን አስብ። ዳግመኛም የላከኸውን አቃንቶ ሲመለስ ይህን አጎደልኸ በማለት አታበሳጨው። እሱ ገንዘቡ ያልሆነውን አይበላምና ያንተም ያልሆንውን ለማምጣት አያዝንልህምና።

ልጄ ሆይ፦ ከባዕድ ሰው ማዕድ መቅረብን አትውደድ (ቀላዋጭ አትሁን) እንዲህ ያለው ነገር ያዋርድሃል ያስንቅሃልና።

“የሌላ ማዕድ ደጅ የሚጠና ተስፋ የሚያደርግ ሰው አነዋወሩ እንደ ሞተ ሰው ነው እንጂ እንደ ደኅነኛ አይደለም የሰው እህል የሚወድ ሰው ከሐሜት አይድንም የተመከረ አዋቂ ሰው ግን ከሁሉ ይጠበቃል።” /ሲራ 40፥29/

ልጄ ሆይ፦ በሕይወት እስካለህ ድረስ የምትኖረው ኑሮ ኃጢአት ለመስራት አይሁን፥ ሞት እንዳለብህ አስብ የምትሞትበት ቀን እንዳለ አስታውስ። (ለሞት ወሬኛ የለውምና) /2ኛ ቆሮ 5፥ 7/

ልጄ ሆይ፦ እግዚአበሔር ባዘዘው ትእዛዝ ካልሆነ አለ ጌታው ፍቃድ ያንተ ያልሆነውን ፈረስ ላይ አትቀመጥ። አንተ ሳታውቅ በገንዘብና በጌትነት ከሚበልጥህ ከታላቅ ሰው ጋር አትከራከር፣ አትጣላ፣ አትሟገት። (ከጥይት አገዳደል የገንዘብ አገዳደል ይከፋልና)።  “እንደ ጌትነቱ መጠን ፍርድን ይለውጡታልና ከዳኛ (ከሹመኛ) ጋር አትከራከር።” /ሲራ 8፥14/

ልጄ ሆይ፦ የቤትህ በራፍ ሰባት ክንድ ያህል ከፍታ ቢኖረውም እንኳን ራስህን ዝቅ አድርገህ ግባ።

ልጄ ሆይ፦ በትንሽ መስፈሪያ ሰጥተህ በትልቅ መስፈሪያ አትውሰድ (አትቀበል)። ይህ በትንሽ መስፈሪያ ሰጥቶ በትልቅ መስፈሪያ መውሰዱ ሀብታም ሊያደርግህ አይችልምና ይልቁንም የነበረህን የጠፋብሃል ድኃ አድርጎም ያዋርድሃል እንጂ።

“እንጠረኛ፥ በብሩ ወርቅ በውርቁም ብርን ባይጨምርበት ከጭንቅ ይድናል። መሸተኛም በውይኑ (በጠጅ በጠላው) ውኃን ባያበዛበት ከዓመፅ ይድናል።” /ሲራ 26፥29/

ልጄ ሆይ፦ ፈላስፋን ያየህ እንደሆነ ጥበቡን ሁሉ ልትውስድ (ልታስቀር) ብትወድ በመታዘዝና በትሕትና ሆነ ተከተለው እንጂ ጥበቡን በቶሎ ለመውሰድ (ለመንጠቅ) በመቸኮል አታጣድፈው።

ልጄ ሆይ፦ አስፈላጊ ጉዳይ ኑሮህ ዓላዋቂውን ሰነፍ ሰው ከምትልክ ይልቅ በርሱ ፋንታ አንተው ራስህ ብትላከው ይሻላሃል። እርሱ ጉዳይህን አያቃናልህምና ካላማቃናቱም በላይ ነገርህን ያበላሽብሃልና።

ልጄ ሆይ፦ ገንዘብን በእጁ ከማስጨበጥህ በፊት ልጅህን አስቀድመህ በምግብ በመጠጥ ሞክረው (ታዘበው)። ደግሞም ገንዘብህን በሀብትም ሆነ በጌትነት ከሚልቅህ ሰው ገንዘብህ ጋር አትጨምረው። ከገንዘብህ ወስዶ ከርሱ ገንዘብ ጋር እንዳይጨምረው። ገንዘቤን እለያለሁም ብትል ተከራክሮና ተሟግቶ ማስመለሱን አትችልምና። ልብህ በኃዘን ሲታመም ሆድህ ሲታመስ ይኖራል እንጂ።

“ለባለጸጋው አታበድረው በታበድረው ግን ገንዘብህን እንዳጣህ እወቅ ባለጸጋውን አትዋሰው ብትዋሰው ግን እንግዲህ አንተ እንደ ከፈልክ አስብ።” /ሲራ 8፥12-13/

ልጄ ሆይ፦ ከዕሬት ይልቅ የሚመሩ ልዩ ለዩ ፍሬዎችን በላሁ ነገር ግን ከድህነት የመረረ ምሬት አላገኘሁም። ዳግመኛም ከባድ ብረትንና እርሳስን ተሸከምኹ ነገር ግን እንደ ብርድ ያለ ከባድ ነገር አላገኘሁም። ነገር ግን በቀድሞዎቹ ሰዎች ዘንድ እንደሆነ ነው እንጂ በዛሬዎቹስ ዘንድ እንደ ብርድ የቀለለ ነገር የለም ለማለት የስደፍራል።

ልጄ ሆይ፦ አለት ደንጊያን ፈነቀልኩ፣ አሸዋንም ተሸከምኩ፤ ነገር ግን ከባዕድ ቤት መኖርን የመሰለ ከባድና ጽኑ ነገር አላገኘሁም። ልዩ ልዩ ጣዕም ያለውን ብዙ ምግብ በልቻለሁ ነገር ግን እንደ ጤና አድርጎ የሚጣፍጥ ነገር አላገኘሁም።

ልጄ ሆይ፦ ምንም ድሃ ብትሆን ምንም ብታጣና በትቸገር ደኅነትህንና መቸገርህን ለማይረዱህና ለማያዝንልህ ወንድሞችህ አትግለጥ። በእነርሱ ዘንድ የተጠላህና የተዋረድኽ ትሆናለህ እንጂ ምን ምን አይሰጡህምና።

ልጄ ሆይ፦ ሚስትህን እንደ ራስህ አድርገህ  ውደዳት። እርሷ የልጆችህ መገኛ ናትና፥ አንተም እንደርሷ ካለች እናት መገኘትህን አስታውስ።

“ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና።” /ኤፌ 5፥28-29/                                                           

ልጄ ሆይ፦ ለልጆችህ መራብንና መጠማትን አስተምራቸው። አድገው ሀብታሞች በሆኑ ጊዜ የተራበውንና የተጠማውን እንዲያስታውሱና የለመናቸውን ቸል እንዳይሉ።

ልጄ ሆይ፦ ከሰነፍ ሰው መጾም የዓዋቂ ሰው ምክር ይሻላል። ከልብ መታውር የዓይን መታወር ይበልጣል፥ ዓይነ ስውር በጎዳና ተመርቶ ይሄዳል ልቡ የታወረ ግን በቀና መንገድ ቢመሩት ተመርቶ ለመሄድ አይችልምና።

“ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን። እናያለን ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።” /ዮሐ 9፥41/

ልጄ ሆይ፦ ከመልካም ቁንጅናና ከመልካም ደም ግባት መልካም ስም ይበልጣል። መልካም መልክና መልካም ደም ግባት ያረጃል፣ ያልፋል፤ መልካም ስም ለዘለዓለም ይኖራልና።

ልጄ ሆይ፦ በሌላ እጅ ከተያዘው ሙሉ (የበግ) ሥጋ በአንተ እጅ ያለው የበግ እገዳ (ቅልጥም) ይበልጣል። እንዲሁም በአየር ላይ ከሚኖሩ ከሺ ወፎች በእጅህ ያለችው አንዲት ወፎ ትበልጣለች። (በሰው እጅ ካለው ብዙ በእጅህ ያለው ጥቂት ነገር ይበልጣል)።

ልጄ ሆይ፦ ሰው በአንደበቱ ሲድጥ በእግሩ ከሚድጥ ይሻለዋል። ለእግር መዳጥ መነሳት አለው ለአንደበት መዳጥ መነሳት የለውመና። (አንደበት ሲያድጥ ከዕዳ፤ እግር ቢያድጥ ከአንጋዳ) እንዲሉ። ልጄ ! አስቀድመህ ከልብህ ሳትማከር (ሳታወጣና ሳታወርድ) ነገርህን ከአፍህ አታውጣ። “በአንደበትህ ከምትሰነካከል በምድር ላይ ብትወድቅ ይሻልሃል።” /ሲራ 20፥ 18/

ልጄ ሆይ፦ ውኃ ተመለሶ ወደ ኋላው ቢሄድ (ቢፈስ፣ ወፎች አለ ክንፍ ቢበሩ፣ ቁራ እንደ በረዶ ቢነጣ፤ ሰነፍ ሰው ዓዋቂ ሊሆን እንደማይችል) ዕወቅ።

“ወይራ ጠማማነቱን ቢተው ነብር ዠንጉርጉርነቱን ቢለቅ እስራኤል ክፋታቸውን አይተውም።” ኤር 13፥ 23-26

ልጄ ሆይ፦ የሴት አማጭ (አዋያይ) መሆንን አትውደድ ሴትየዋ ክፉ ትሁን ደግ ትሁን አታውቅምና። ክፉ የሆነች እንደሆነ በራስህና በልጆችህ ላይ መርገምን ታተርፋለህ። (አንተ አታላይ፥ ልጆችህ  የአታላይ ልጆች እየተባላቹህ ስትከሰሱና ስትወቀሱ ትኖራላቹ ማለቱ ነው)።

ልጄ ሆይ፦ እንዳይሰለቹህ ወዳጆችህን ቶሎ ቶሎ መጎብኘትን አታብዛ እንዳይረሱህም ፈጽመህ ከእነርሱ አትራቅ።

“እንዳይሰለችህ፥ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘወትር።” /ተግ 1፥ 17/

ልጄ ሆይ፦ ሥር - መሠረታቸውን ጠባያቸውንና ታሪካቸውን ሳትመረምር እንዲያሁም አፍአዊ ሀብታቸውንና ልብሳቸውን አይተህ ባለጸጎችን ወዳጆች አታድርግ።

“ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” /1ኛ ሳሙ 16፥ 7/

ልጄ ሆይ፦ ከጠላቱ ጋር የሚወዳጅና ኃጢአቱን (ምስጢሩን) የሚገልፅ ሰው የጥልን በር ከፈተ። ከጠላት ጋር መወዳጀት ልብን የሚያናድድ የጥል በር ይከፍታልና።

  .................................................... ተፈጸመ ...................................................
ዋቢ መፅሐፍ:- አንገረ ፈላስፋ (የፈላስፋዎች አነጋገር) በሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ

No comments:

Post a Comment