Saturday, August 24, 2013

“አዳም የት ነህ?” በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)


ከሩቅ ይሰማኛል
የቤተ- ክርስቲያን ደውል

ነፍስን የሚያማልል
ልብን የሚያባብል

እንደ አዲስ የሆነ
እንደ አዋጅ የሆነ
ከቀኑ ሁሉ ጠዋት እሁድ የገነነ
ከእለት ሁሉ ግህዝ እሁድ የገነነ

ማለዳ ሰንጥቆ የሚያስገመግም
ሠመመን መሳይ ድምፅ ከሩቅ ሚሰማ
ቀላቀሎ የያዘ የካህናት ወረብ የካህናት ዜማ

ንፋስ የሚያመጣው አልፎ-አልፎ ሽው የሚል
ተነስ ቀድሰ የሚል አዳም የት ነህ የሚል


አፍላ ጠዋት ሆኖ ሠማይ ከመሬት ጋር ሊላቀቅ ሲደማ
ሮች እንዳጤዙ ምንጩ ሳይነከር ቀኑ አዲስ እንዳለ
ከማለዳ ወፎች ድምፅ በልጦ
ከንፋስ ከሚጋጩ የዛፎች ድምፅ በልጦ

ከሩቅ የሚመጣው የደውል ቤት ጩኸት የካህናት ዜማ
አየሩን ሰንጥቆ ንጋት ላይ ሲሰማ

ተንሰኡ ሲል ገና ልቤን አሽፈተው
የቆየ ስሜቴን ማህሌት ያደረ የቄሳር ሸተተው
ደግሞ ያ ምስላቸው የቄሶች አቋቋም አደራደራቸው
የተክለ-ዝማሜ ሸምበቆ ስልታቸው

በዓይነ-ህሊናዬ ድቅን እያለብኝ ቅዝዝ ያደርገኛል
............................................ አዳም የት ነህ ይለኛል

እንዲህ ሲነጋጋ እሁድ ሊሆን ቀኑሠማይ ወገግ ሲል
ከደብሩ ምሶሶዎች ከውስጠኛው ፍል

ከታቦት ማደርያ ከአንጎበር ክፍልፋይ ከጣሪያው ሥዕል
ልቆ ለመሰማት በሚጠር ትናጋ የዜማ ውድድር
በአንገታቸው ዙሪያ አግድም ባሰመረው የቄሶቹ ደም-ስር
የሽቅም ተገፍቶ የሚወጣው ዜማ ...
ጩኾ ... ንሮ፥ ንሮ
ልቆ ... ንሮ፥ ንሮ

ድንገት ፀጥ እያለ በሚቆየው ፋታ
የእጣነ መጎሩ ወዲህ-ወዲያ እንክርት ልዩ ቅጭልጭልታ
በመሐል ብቅ ሲል የሚሰጠው ሠላም የሚፈጥረው ደስታ

በጆሮዬ ነፍሶ አሁን እስኪመስል ድንግጥ ያደርገኛል
................................................... አዳም የት ነህ ይለኛል

ወዲያውኑ ደሞ ድንገት እጣን በነካካ የካህናት መዳፍ
ተገለጦ ከተኛው የብራና መጻፍ
ከቀይና ጥቁር ፊደላት ቆሎ
በዓይን እየዘገኑ ላንቃ ላይ ወርውሮ

ከሠማያት አምባ ከአርያም ሠፈር
ተጭኞ በደመና በዜማ መሳፈር
መሄድ፥ መሄድ፣ መሄድ፣ መሄድ ያሰኘኛል መዝለቅ ከአድማሱ ስር
............................................................ ከፀባዎት አምባ ከአርም ቅጥር

ብቻ እንደ ጥንቱ ለመሆን ያምረኛል
ያኔ ቅስናዬ ሳይፈርስ ለብዙ ዘመናት በድንግልናዬን እንደጸናሁ ሁሉ
ሠርክ ሳደገድግ ከደብር ሳልጠፋ
ከቅዳሴ ምላሽ ከጸበል ዳር ቆሜ ድዌያንን ላሰልፍ ስደክም ስለፋ
ነፍሴን ላለመልም ስጋዬን ሳረትም እንደኖርኩት ሁሉ እንደ ያኔው ሁሉ ያምረኛል

ደግሞ በአፍላነቴ በልጅነቴ ጊዜዬ በማለዳ ነቅቼ
በሣር ውስጥ መሐል ባለ ቀጭን በልጅ እግሬ እሮጬ
ከደብሩ ጉብታ ከደውሉ ቤት ሄጄ
በላብ የጠቆረ ገመድ ስወዘውዝ
እጄ አለደርስ እያለኝ በእግር ጣቴ ቆሜ የቤቱን ወጋግራ ጉት ፈልጌ ስይዝ
ያ በልጅነቴ የሆንኩት አካዋህኔ ሁሉ ድቅን ይልብኛል
.................................................. አዳም የት ነህ ይለኛል

ዳሩ ምን ሊፈይድ የከሰመ እጣ
ጊዜ አልፎበት ጡኡምነቱን ያጣ
አውራጅ ያጣ ንቋጣ

መቼም ይህቺ ሕይወት መስቀሏ ብዙ ነው
ታግላ ላትረታ ፀሯን ላታስገበረው
ከዓለም ጋር ግብ-ግብ ትወዳለች
ተመንትፋ ሳትሄድ ለኑሮም ሳትመች

ዛሬማ እኔ ቅስናዬ ፈርሶ
ድንግልናዬ ተድሶ
ጥምጣሜን ከፈታው ስንት ዘመን አለኝ
እንደው ብቻ ድንገት የጠዋቱ ደውል ማለዳ ቀስቅሶ አዳም የት አለኝ

እናም አውቆ የተኛን ሠው አይሰማም እንዲሉ
የዛሬውን ደውል አልሰማውም አሉ
የኔ ትዝታዎች የድሮ ቀኞቼ ዝም በሉ

ልቤ እንዳደላቹ ለስጋዬ እንዳሁን ዓለም ቁብ እንዳላት
ምትመለስባት ለነፍሴም ቀን አላት
ያ እስኪሆንላት ... ይህ እንዳይብስባት
የድሮ ቀኖቼ እየነካካቹ ... አትሁንብኝ ጠላት

ልሸፋነንና አውቆ ልተኛበት የዛሬውን ደውል አልሰማሁም ልበል
የደብር እድገቴ የቄሱ ሁኔታዬ ትዝን ዝም በል
ግን ከሩቅ ይሰማኛል የቤተ-ክርስቲያን ደውል
ነፋስ የሚያመጣው አልፎ-አልፎ ሽው የሚል
ተነስ ቀድስ የሚል ... አዳም የት ነህ የሚል


(ምንጭ፦ ከቴ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የነ-ግጥም ራዎ ውስጥ፤ ከዩቱብ፦ ከምስል ወ ድምጽ ጹሑፍ ጻፍኩት።)


No comments:

Post a Comment