Sunday, January 26, 2014

መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ! /1ኛ ቆሮ ፪፥፲፫/

         እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ አድሮ መንፈሳዊውን ቃል የሚያናግረን፣ መልካም የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ሐሳብና እንድንማማር የሚያደርገን እርሱ ባለቤቱ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዘመነ ልቦና እስከ ኦሪት ድረስ ስለ ድንግልና በሰፊው ከሚያትቱልን ዓበይት ክፍል አንዱ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ ነው። ስለ ርብቃ፥ ድንግልዋን ጠብቃ ስለመኖሮ፦ "ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች" ይላል። /ዘፍ ፳፮፥፲፬/ እንዲሁም፥ ስለ ዮፍታሄ ልጅ ስለ ድንግሊቱ፤ /መሣ ፲፩፥፴-፵/ በአጠቃላይ ስለ ድንግልና ጠበቆ መገኘትና ድንግልና ጠበቆ አለመገኘት፤ በእግዚአብሔር ዘንድና በእስራኤላውያን እምነትና ሃይማኖት አንፃር ምን ያህል ትልቅ ሥፍራ እንዳለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በዘ ዳግም ምዕራፍ ፳፪ ከቁጥር ፲፫-፳፰ መመልከት፤ ማንበብና ማገናዘብ ብልህነት ነው እግዚአብሔር በነቢያት አንደበት አድሮ ትንቢቱንና የእግዚአብሔር ልጆች በሕይወታቸው ምን መምሰል እንዳለባቸው በተለያየ ጊዜያት ተናግሯል። በሐዲስ ኪዳንም፥ ስለ ድንግል ማርያምም በነቢየ ኢሳያስ ቀን አስቆጥሮ፣ ትንቢት ተናግር፦ "ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።" /ኢሳ ፯፥፲፬/ ተብሎ የተተነበየው ትንቢት ጊዜውና ሰዓቱ ሲደርስ "እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።" /ማቴ ፩፥፳፫፤ ሉቃ ፩፥፳፯/

ለማጠየቅም፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፤ ወደ ገላትያ በላከላቸው ክታቡ ላይ፦ "ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ" በማለት፤ "ሴት" ብሎ ስለ እናቱ ድንግሊቷ ድንግል ማርያም፣ "የተወለደውን ልጁን" ብሎ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገልፃቸዋል።

ሌላውና ዋናው ርዕሰ-ጉዳዬ "የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" /ማቴ ፩፥፳፭/ የሚለው ሐረፍተ ነገር (ቃል) ነው። እራሳቸው ስተው ሌላውን ለማሳት ደፋ ቀና የሚሉ ሠዎች፦ ይህንንም አሳባቸውን እንዲያጠናክርላቸው "አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች።" እና "ቃየንም ሚስቱን አወቀ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች።" /ዘፍ ፬፥፩ እና ፲፯/ በማለት ታላቅ የሆነ የስህተተ ስህተት፤ የጥፋት ጥፋት እየሠሩ ይገኛሉ። በመቀጠልም የልባቸውን ምኞት ለማሳካት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በማለት፦ "እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" ካለ ከወለደች በኋላ አወቃት ማለት ነው፤ በማለት የተዛባ ትርጓሜ ያክሉበታል፤ እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን!

         ለመሆኑ እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እንደሚገልጹት መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ብንመረምር እንኳን፤ "አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች።" እና "ቃየንም ሚስቱን አወቀ ፀነሰችም፥ ሄኖሕንም ወለደች።" የሚሉትን በመጥቀስ "እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" የሚለውን ለማገናኘት ሲሞክሩ እናያለን።

እንደ አዳምና እንደ ቃየን ሚስቶቻቸውን እንዳወቋቸው (በሩካቤ ሥጋ) ጻድቅ ዮሴፍንም "እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" እና "ከወለደች በኋላ አወቃት" ብሎ መናገርና መፃፍ፤ ስለ ብዙ ነገሮችና በትንሹ ስለ አራቱን ዋና ዋና ነገሮች የማይሄድና የማይስማማ ሆኖ እንገኘዋለን።

፩ኛ፦ እጮኛ እንጂ ሚስቱ አለመባሏ፤ (በእስራኤላውያን ዘንድ በባልና በሚስነት እንጂ፤ በእጫኝነት ጊዜ ሚስት ወይም ባል ማለት ነውር ነው።)
፪ኛ፦ ሚስቱን አወቀ የሚል ጥሬ ቃል አለመኖሩን፤ (አዳም ሚስቱን አወቀ እንደሚለው)
፫ኛ፦ ካወቃት በኋላ ፀነሰችም፥ አለመባሏ፤ ( ሔዋን ፀነሰችም እንደተባለችው)
፬ኛ፦ ሴትም ይሁን ወንድ ልጅ ወለደች ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ አለመመዝገቧ፤ ( እንደ ሔዋን፦ ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች።)

ከላይ የጠቀስኳቸው ድንግል ማርያም ሌሎች ልጆች አለመውለዷን፣ የሚያመላክቱ፥ እውነት ያለውና በምንም መልኩ መልስ የማይገኝለት ምልከታ ነው። ለእነዚህ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በፈቀደልኝና ባመላከተኝ ሁናቴ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮን "መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም።" /1ኛ ቆሮ ፪፥፲፫/ በሚለው መሠረት ተመርኹዤ መጽሐፍ ቅዱስ ቃልን ልመርምር።

ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ማስተማርና ዕድሜ ሲናገር፦ "ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር" /ሉቃ ፫፥፳፫/ ብሎ መዝግቦልናል። ከዚህ ከመዘገበልን የዕድሜ ገደብ ተነስተን፥ ጌታችን ወደ ተወለደበት ወደኋላ ተመልሰን ስናሰላ የእናቱን የድንግል ማርያምን ዕድሜንም አብረን እናሰላለን። (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ድንግል ማርያም በዚህ  ምድር በሕይወተ ሥጋ ሦስት ዓመት ከእናት አባቷ ቤት፣ አስራ ሁለት ዓመት በቤተ-መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን ፀንሳ፣ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር፣ አስራ አምስት ዓመት ከዮሐንስ ቤት በአጠቃላይ ስድሳ አራት ዓመታት ያህል ቆይታ በክብር አርፋለች፡፡ እመቤታችን ያረፈችው፥ በጥር ሃያ አንድ ቀን 50 / ገደማ ነው።)

ቢሆንም ግን "መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ" የሚሉ ወገኖች ስላሉ የዕድሜ ዳሰሳውን በመተው ጌታ ማስተማር ከጀመረበት ጀምሮ እስከ ተወለደበት ዕለት ሠላሳ ዓመት በእናትነት አብራው እንደነበረች እንረዳለን ማለት ነው። (ጌታችን፥ ያስተማረበትን ስንደምረው፤ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ይሆናል ማለት ነው።) ይህም የሉቃስን ወንጌል መነሻችንን በማድረግ መንፈሳዊ ምርመራዬን እቀጥላለሁ።

እንደምናውቀ ቅድስት ድንግል ማርያም፥ መድኃኒታችንን፣ መድኅነ ዓለምን ኢየሱስ ክርስቶስን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደወለደችው የታወቀ ነው። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከድንግል ማርያም ጋር፥ ከልደት እስከ ግብፅ ስደት፣ ከግብፅ ስደት ወደ አገረ እስራኤል መልስ፣ ከእስራኤል መልስ እስከ ጥምቀት፣ ከጥምቀት እስከ ማስተማር ድረስ እናቱ ማርያምም ሁሉን ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር።

እራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ስለ ግብፅ ስደት በሚተርክበት ከምዕራፍ ሁለት ጀምሮ፦ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ እናቱና ስለ ጻድቁ ዮሴፍ በተናገረበት አንቀፅ "የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው።" /ማቴ ፪፥፲፫/ ይላል። አንባቢያን ሆ ይ፦ እዚህ ጋር አስደናቂ እንገነዘባለን፤ ይኸውም፦ ጻድቁ ዮሴፍ ለድንግል ማርያም፥ እንኳን ለሚስትነት ደረጃ ይቅርና የእጮኝነት አስተሳሰብ፣ ንግግርና ቃል፤ እንዳልተነገረ ከዚህ ምዕራፍ ጀምሮና በቀጣይ ምዕራፎች ጠቅሶትና ተጠቅሞበት አናገኘውም። ይልቅ፦ ወደ ግብፅ ከመሰደዳቸው ጀምሮ ወደ እስራኤል አገር እስከገቡበት ድረስና እስከ ክርስቶስ ስቅለት ድረስ ቢሆንም "ሕፃኑንና እናቱንም፤ እናቱም" /ማቴ ፪፥፲፫-፳፩፤ ፴፫፤ ፶፩/ በማለት በመደጋገም ሲጠቀምበት እንደነበረ ህያው የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

በእዚች ምድር መድኃኒታችን መድኅነ ዓለምን ኢየሱስ ክርስቶስን ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ተምረን እንድናስተምር፥ ተምሮ አስተማረን፤ የሕይወት ስንቅ፥ ምግብና መጠጥ የምናገኝበት አመላከተን (አሳየን) አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን እንዳሳያቸውና በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ በመንፈስ ቅዱስ እንደተጠመቁ (እስከወረደላቸው) /ሐዋ ፩፥፫፤ ፪፥፩-፬፯/ ድረስ አንድ ጎበዝ ሕይወቱን ሙሉ ህገ እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ እያለ ክርስቶስንና የክርስቶስ የሆኑትን፥ የሚያሳድድ፣ የሚያስር፣ የሚያንገላታ፣ በመግደል ቢሆን የሚስማማ፣ ቤተ-ክርስቲያንን ያፈርስ፤ ሳውል የሚሉት ሰው ነበረ።

ይህ ብርቱና ጎበዝ ሠው፥ "ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት እየሄደ ሳለ ነበር በምድርም ላይ ወድቆ የወደቀው። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ከመንበረ ጸባዖት ሰማ። በዚህ ድምፅ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ ተቀበለና ቀዳማይና የተመረጠ ዕቃ እንዲሁም ስሙ ተቀይሮ ጳውሎስ እስከመባል የበቃ ታላቅ ሐዋርያው ሆነ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስን ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወርን፥ የእናቱን፣ የትውልዱን፣ የግርፋቱን፣ የስቅለቱን፣ የሞቱን፣ የትንሣኤውና የዳግም ምፅአቱን አጠቃላይ ብሉያትንና ሐዲሳትን በማዋሃድ (በማበሰጣጠረ) በሰፊው አስተምሯል። ከእነዚህ ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ካስተማራቸው ለቆሮንጦስ ምዕመናን "በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤" /2 ቆሮ ፲፩፥፪/ ብሎ አስተምሯል። አሁንም ወንድሞች ሆይ፦ ልብ ልንለው የሚገባው ዓብይ ዕርሰ-ጉዳያችን "የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" /ማቴ ፩፥፳፭/ የሚለውን ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደ ከሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በኋላ የተነሳ ሐዋርያ ነው። ይህ ሐዋርያ ምን ቢያነብ? ነው ምንስ ቢገለፅለት ነው? የክርስቶስን እናትን "እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና" ያለው ከየት አምጥቶት ይሆን? ወይስ ለራሱ ጥቅም ይሆን ወይ? አልያም እንደናንተ "የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" ከወለደች በኋላ ግን አወቃትና ወለደች ማለት ነበረበትን? ለምንስ መዋሸት ከጀለው። ለምንስ የእስራኤልን የድንግልናንና የንጽሕናን ህግ እያወቀ እናንተን "እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና" ማለቱና የእግዚአብሔርን ቃል መሻሩ ስለምን አስፈለገው? ይህ ጥያቄዬ ለሐሰተኞች ወንድሞችና እኅቶች ነው።

        እኛስ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ ሁለት ቁጥር ሃያ አምስት "የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም" የሚለውን ጻድቅ ዮሴፍ ቢያቃት ኑሮማ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና" ባላለን ነበር። ጻድቅ ዮሴፍ እስከ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መነሳት ድረስ እንዳላወቃት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በማያሻማ ቃል ይገልፅልናል። ይህም ማለት ክርስቶስን እስክትወልድ ድረስና ከወለደችም በኋላ እንዳላወቃት ይመሰክራል።

በተጨማሪም፦ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ጌታን ፀንሳ የመውለጃዋ ወራት በደረሰ ጊዜ ከወለደችበት ደቂቃና ሠዓታታ አንስቶ እስከ ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ድረስ በንጽሕናና በድንግልና እንደነበረች ሐዋርያው አስረድቶናል። በመቀጠልም፥ ወንድሞቹ የተባሉትም ከእርሷ እንዳልሆነም እንገነዘባለን ማለት ነው። ምክንያቱም፥ ወንድሞቹ የተባሉት፣ ለሥም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ከጀመረ በኋላ ነው። ማስተማር የጀመረው ደግሞ በሠላሳ ዓመቱ እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል። ስለዚህ እነርሱ ሐሰተኞች ወንድሞችና እኅቶች የሚያቀርቧቸው የሐሰት ትምህርታቸው መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ተቀባይነት አያገኝም ማለት ነው።

እውነት ነው እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም!!! እናሳ ከወለደች ላስ እንዴት አወቃት?

አቤቱ ጌታችን ሆይ፦ ተቀዳሚ ተከታይ ስለ ሌለው ስለ ልጅህ ስለ ወደዳጅህ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አማኑኤል ብለህ ይቅርታህን ከኛ አታርቅ፤ መሐላህንም አታፍርስ በእውነት ያለሐሰት።

በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልውና ሆነው የሚኖር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ። በሱም አብ መንፈስ ቅዱስ ህልውና ሆነው የሚኖሩ። ልቦናው አብ፣ ያንደበቱም ትንፋሽ መንፈስ ቅዱስ፤ የሚሆን ኢየሱስ ክርስቶስ። እርሱም የአብ የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው የሚኖር ኢየሱስ ክርስቶስ።

በልዕልና ሳለ በመሠረት ያለውን የሚያይ። በውነት ከሰማይ በቸርነቱ ወርዶ ክብርት ድንግል ከምትሆን ከእመቤታችን በሰው ሥጋ ተወለደ። ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ ተወስኖ፣ ልጅነትን ሰጥቶ፤ በሥጋው ወገኖቹን ያደርግ ዘንድ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ልደቱ ነገር እንዲህ ነው፦ እናቱ እመቤታችን ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ድንጋሌ ሥጋ ድንጋሌ ነፍስ ስላት። ከማየት፣ ከመስማት፣ ከመናገር፣ ከመዳሰስ፤ ድንግል ስትሆን።

ዕጮኛዋ ዮሴፍ ግን ደግ ሰው ነውና ሊገልጣት፣ ሊያጣላት አልወደደም። ሰውሮ ሊያኖራት ወደደ እንጂ! ይህንንም ሲያስብ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፣ በሕልምም ተነጋገረው። የዳዊት ልጀ ዮሴፍ ሆይ ዕጮኛህ ማርያምን መቀበል አትፍራ። ከሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና። እነሆ፦ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም ኢየሱስ (መድኃኒት) ትለዋለች። እሱ ወገኖቹን ከኃጢአታቸው ፍዳ ያድናቸዋልና። ይህ ሁሉ የተደረገው፥ ነቢይ ከእግዚአብሔር አግኝቶ፤ እነሆ፦ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል ብሎ የተናገረው ይደርስ፣ ይፈጸም ዘንድ ነው።

አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከኛ ጋር የሆነ ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ተነሥቶ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ ዮሴፍም ለድንግልናዋ ሰገደ። ለንጽሕናዋ፣ ለቅድስናዋም። ተገዛ። ዕጮኛው የምትሆን ማርያምንም ወሰዳት። በኵር ተብሎ የተጠራ ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም። (ጻድቁ ዮሴፍ እመቤታችንን ድንግል ማርያምን፦ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና የመውለዷ ምስጢር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት መሆኗን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፣ አልተረዳም ነበር።) /ድርሳነ ማሕየዊ ምዕ ፲፫-፴፰/

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወድንግል ማርያም ክብር!!!

No comments:

Post a Comment