Sunday, January 19, 2014

የጥምቀት ጥልቅ ምስጢሩ

ዛሬ ገሃድ ነው፥ የጌታ ዕጹብ ድንቅ ሥራ፤
ዓለም እንዲያውቀው፥ የአምላክ ብርሃን በራ።

አብ በደመና፥ በክብር ተገለጠና፤
ክርስቶስ፥ በዮርዳኖስ ተጠመቀና፤
የሠላም ርግብ፥ መንፈስ ቅዱስ መጣና፤
የሦስት አካላት፥ ምስጢር ተገለጠና።

ትልቋ ባህር አየች፥ ሸሸች፤
ዮርዳኖስም፥ ወደኋላ ተመለሰች፤
ኮረብቶች ዘለሉ፥ እንደ ጠቦቶች፤
ንዕማን ከለምጹ፥ ኢዮብን ከቁስሉ አዳነች።

ከደማስቆ ወንዝ ይልቅ፥ በዮርዳኖስ ተጠምቀው ቢውሉ፤
ከያዕቆብ አምላክ ፊት፥ የምዕረት ብርሃን ተቀበሉ።

የጥምቀት ጥልቅ ምስጢሩ፥ መዳኛ ነው፤
በወንጌል የተጠመቀ፣ ይድናል እንደተባለው፤
አይሁድ አለቃ፥ ለኒቆዲሞስ የተነገረው፤
እግዚአብሔር መንግሥት መውረሻ ነው።

የሥላሴ ልጅነት የሚገኝበት፥ እያው ምስጢር፤
ጥበብ አለን፥ አወቅን ከሚሉት ሲርቅና ሲሰወር።

ጌታም አለ፦ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤
ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ፥ እንዴት ታምናላችሁ?።

እወነቱ ይሄ ነው! እኛም ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለድን፤
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት፥ ልንገባ እንዳይቻለን፤
የድንግል ልጅ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አስታወቀን፤
እነሆ፦ በጥምቀት ከእርሱ ጋር እንተባበራለን።

ዛሬ ገሃድ ነው! የጌታ ዕጹብ ድንቅ ሥራ፤
ዓለም እንዲያውቀው፥ የአምላክ ብርሃን በራ።

(እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!!)

No comments:

Post a Comment