Monday, April 6, 2015

ሆሣዕና በአርያምና የካህናት አለቆችና የጻፎች ክስ (ማቴ ፳፩፥፲፭-፲፮)



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

አንዳንድ "ክርስቲያን ነን" ባዮች፤ እንደ ካህናት አለቆችና ጻፎች ተቆጥተው፦ "ሆሣዕና ምንድን ነው?" የሚሉ፣ እናውቀናለን ብለውም አላዋቂነታቸው የተቆጡበት የኑፋቄ ቃላቸውና ድምጻቸው ያስታውቃል።  የዘመናችን የካህናት አለቆችና ጻፎችም ኧሊህ ናችው! ከአስመሳይነት ውጭ ኢየሱስን እንኳን በምዕሉ በጥቂቱም ኧረ እንደውም እጅግ በጥቂቱ አያውቁትም!

ለዚህም ነው የዛሬዎች የካህናት አለቆችና ጻፎችም፦ «ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቆጥተው» "በኦርቶዶክስ እምነት እንዲህና እንደዚህ ታደርጋለች" እያሉ፤ በአምላካችንና በመድኃኒታችን፣ በመድኅነ ዓለም በክርስቶስ ፊት ሊከሱን ያደባሉ፤ ዳሩ ግን መጥምቀ ዮሐንስ እንዲህ ተብሏል፦ «ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም፥ አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።» (ማቴ ፫፥፯-) ተብሎ የተፃፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? በእውኑ ይኼ ድንጋይ ምንድን ነው? ከድንጋይስ፥ ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል የተባለውስ ምንድን ነው? ደግሞስ የተፈጥሮ ድንጋዮች አመሰገኑት ወይ? ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት በድንጋዮች አንፃር የተነገረውስ እነማን ይኾኑ? ከሳሽና ወቃሽ ድሮም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ! የአብርሃም ልጆች ድንጋዮች ይኾኑ ወይ? ለዚህ ምላሽ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይለናል፦
 
የሕይወት ቃል፣ እውነተኛው የሃይማኖት ምስክራችን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል። የዘንባባ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡና። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው እያሉ ጮኹ።» (ዘካ ፱፥፱፤ ማቴ ፳፩፥፱-፲፭፤ ማር ፲፥፱-፲፤ ዮሐ ፲፥፲፫)

በሌላ በኩል ደግሞ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች በልበ አምላክ በነቢየ ዳዊት ትንቢት የተተነበየውን የትንቢት ቃል እያነበቡት አልገባቸውም፣ የትንቢቱም ፍጻሜም እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ «ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት። አቤቱ፦ እባክህ፥ አሁን አድን፣ አቤቱ፦ እባክህ፥ አሁን አቅና። በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ እግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ።» (መዝ ፰፥፪፤ ፻፲፯፥፳፭-፳፮) ተብሎ ተጽፏል።

        በሆሣዕና ዕለት፥ የካህናት አለቆችና ጻፎችም ክስ፦ እያነበቡ አልተረዱትም፣ "አብርሃም አባት አለን" (የዛሬዎቹ ደግሞ ኢየሱስ ብቻ) ከማለት ውጭ ያነበቡትን ወደ ተግባር ሲደረግ ሲያዩ እየተቆጡ፣ የአምልኮ ኃይል አጡ፣ ለማመን አቃታቸው፣ ለዚህም ነው፥ የተነገረውና የተተነበየው ትንቢቶች ሲፈጸም የተመለከቱት የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዲህ ብለው አጉረመረሙ፦ «ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፤ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።» (ማቴ ፳፩፥፲፭-፲፮) በእርግጥም "ክርስቲያን ነን" ባዮች እንደ ካህናት አለቆችና ጻፎች ተቆጥተው፦ "ሆሣዕና ምንድን ነው?" ብለው ሲጠይቁ፤ አንብበናል ቢሉም ዳሩ ግን በነቢያትና በመዝሙራት፣ በትንቢትና በወንጌል የተጻፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? እንላቸዋለን።




«ሆሣዕና በአርያም» ክብርና ምስጋና ድንግል ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይኹን! አሜን። (ማቴ ፩፥፳፫፤ ፳፩፥፱)

No comments:

Post a Comment