
እኔ መጀመሪያ ሰው ነኝ፡፡ የተፈጠርኩትም ሰው ሆኜ ነው፡፡ አምላክም የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ቡድን፣ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ጎሳ፣ ነገድ የሚባሉ ነገሮችን ፈጠረ የሚል መጽሐፍም ትምህርትም አላገኘሁም፡፡ ክብርም፣ ሥልጣንም፣ ጥበብም፣ ፈጣሪውን መምሰልም የተሰጠው ለሰው ነው፡፡ መላእክት ሲፈጠሩ በማኅበር ነው የተፈጠሩት፡፡ አንድ ላይ ነው የተገኙት፡፡ ሰው ግን ሲፈጠር በየተራ ነው፡፡ መጀመሪያ አዳም፣ ከዚያ ሔዋን፣ ከዚያ ቃየል፣ ከዚያ አቤል እያለ ተራ በተራ፡፡ ቡድኖቹን ሰው በኋላ ራሱ ፈጠራቸው እንጂ አብረውት አልተፈጠሩም፡፡

መጀመሪያ ሰው ስለነበርኩ መጀመሪያ ሰው ነው መከበር ያለበት፣ መጀመሪያ ሰውነቴ ነው መብት የሚያስፈልገው፣ ሰውነቴን አሥረህ፣ ገርፈህ፣ ገድለህ፣ ነጥቀህ፣ ቀምተህ ቡድኔን ከየት ታገኘዋለህ? እኔን ትተህ እንዴት እኔ ለፈጠርኩት ቅድሚያ ትሰጣለህ? እኔን ንቀህ እንዴት እኔነት ተሰባስቦ ላቋቋመው ቡድን ክብር ትሰጣለህ? ይኼማ ሐሰት ነው፡፡ ሴሎቹን ገድለህ ሰውየውን ማኖር ትችላለህ? ገጾቹን ገንጥለህስ መጽሐፉን ታኖራለህን? ከብቶቹን አርደህ ስለ መንጋው መጨነቅስ ምን ማለት ነው?