፩፦
« መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፤» ዕብ ፲፫፥፬
ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ጋብቻ የእግዚአብሔር ጸጋ
ነው። ስለዚህ በዓይን ምኞት ተጋርደው፥ በሥጋ ፍላጐት ተነድተው ፥ በስሜት ፈረስ ጋልበው ፥ የሚገቡበት ሳይሆን ፦ በጸሎት እና
በምልጃ ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠይቀው የሚፈጽሙት ታላቅ ምሥጢር ነው።
ጋብቻ የሰው ሁሉ ሕልም ነው። የማይመኘው፥የማይፈልገው የለም። የሰው ሁሉ ጸሎት፥ የሰው ሁሉ ስእለት ነው። ለመሆኑ፦ ህልሙ የተፈታለት ፥
ጸሎቱ የደረሰለት ፥ ስዕለቱ የሰመረለት ስንቱ ይሆን? ያላገባው ይናፍቃል ፥ ያገባው ደግሞ ያማርራል። ከጋብቻ በፊት « መልአክ
» የተባለ የትዳር ጓደኛ ከጋብቻ በኋላ «ሰይጣን» ይባላል። «እኔ የመረጥኩትን ካላገባሁ እሰቀላለሁ፤» እንዳልተባለ
«ካልተፋታሁ መርዝ እጠጣለሁ፤» ለማለት ችግር የለም። ከጋብቻ በፊት ምክር ላለመስማት አሳብ ላለመቀበል፦ «ስለ እኔ ማንም
አያገባውም፤» ተብሎ በር እንዳልተዘጋ ሁሉ ከጋብቻ በኋላ ግን ጣልቃ የማያስገቡት ሰው የለም ፤ «ምን በወጣህ ፥ ምን በወጣሽ፤» የሚለውን ፈጥኖ ለመቀበል በሩ
ለሁሉም ክፍት ነው።
፪፦ ጋብቻ እንዴት ተጀመረ?
፪፦ ጋብቻ እንዴት ተጀመረ?
ጋብቻ በአዳምና በሔዋን እንደተጀመረ የጎላ፥ የተረዳ ፥ የታወቀ
ነገር ነው። «ተባዕተ ወአንስተ ገብሮሙ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ » እንዲል፦ አዳም ሲፈጠር ሔዋን በውስጡ ነበረች።
ዘፍ ፩፥፳፰። ይህም በባህርዩ ነበረች ማለት ነው። አንድ አካል፥ አንድ ሥጋ ከሚያሰኛቸው ምሥጢር አንዱና ዋነኛውም ይኸው ነው።
ጋብቻ የተጀመረው በአዳም ጥያቄ ነው፤ ጥያቄዎም የኅሊና ማለትም
ውሳጣዊ ነበር። ምክንያቱም፦ ከላይ እንደተ መለከትነው፦ የትዳር ጓደኛው በውስጡ ስለነበረች ነው። « እግዚአብሔር አምላክም፦
ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፥አለ፤»ይላል። እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱ፦ በአዳም
ኅሊና ውስጥ ይህ ጥያቄ እንደሚነሣ ስለሚያውቅ ነው። መናገሩም ለአዳም ኅሊና እንጂ ፥ ሔዋን ለአዳም እንደምትፈጠርለት አስቀድሞ
በእግዚአብ ሔር ዘንድ የተወሰነ ነው።
እግዚአብሔር፦ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ፦ ሕያው ነፍስ ላለውም ሁሉ ስም ያወጣላቸው
ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው። ይላል። ሂደቱም እንደሚከተለው ነው። እግዚአብሔር ዓርብ በነግህ አዳምን ከፈጠረ በኋላ ቅዳሜ መፍጠሩን
ተወ። እሑድ እንስሳትን አራዊትን አመጣለት ፤ ሰኞ ማክሰኞ አዕዋፋትን አመጣለት፤ ረቡዕ በየብስ የተጠፈጠሩ ፍጥረታትን
አመጣለት፤ ሐሙስ በባሕር የተፈጠሩ ፍጥረታትን አመጣለት፤ ለሁሉም ስም አወጣላቸው። በዚህን ጊዜ አዳም፦ ሁሉም ተባዕትና አንስት
(ወንድና ሴት) መሆናቸውን አይቶ ፦ « ከእኔ በቀር ብቻውን የተፈጠረ የለም፤» ብሎ አዘነ። «ነገር ግን ለአዳም እንደ እርሱ
ያለ ረዳት አልተገኘለትም ነበር ፤» ይላል።
፪
፥፩ ፦ ሐዘነ አዳም፤
እግዚአብሔር አዳም እስኪያዝን የጠበቀው ያለ ምክንያት አይደለም። አጭቶ፥ ወድዶ፥ ፈቅዶ
እንዲገባበት ነው። ይህም፦ ወደፊት ሔዋን ስታሳስተው ለኃጢአቱ እግዚአብሔርን ምክንያት እንዳያደርግ ይጠብቀዋል። አዳም ሳያዝን
ሔዋንን ፈጥሮለት ቢሆን ኖሮ፦ « ይኼ እግዚአብሔር ፍጠርልኝ ሳልለው ሔዋንን ፈጥሮ ምክንያተ ስሕተት ሆነችብኝ፤» ባለ ነበር።
እግዚአብሔር ግን አዳም እስኪፈልግ ጠብቆ ፦ ከጎኑ አንዲት አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራለት። አዳምም፦ «ይህች አጥ ንት
ከአጥንቴ ናት ፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥
ከሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።» ብሎ እግዚአብሔር የሰጠውን በጸጋ ተቀበለ። ዘ፪፥፲፰-፳፬።