Friday, December 20, 2013

ሥራህን ሥራ፦ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ



ሥራህን ሥራ፦ ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰቶታል፤ ያንን መስራት የእሱ ፈንታ ነው። ቢቻለው እሱን ማገድ የዲያብሎስ ሥራ ነው። በርግጥ ሥራውን እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይጥራል። ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል፤ በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል። የሃሜት ጎርፍ ያስወርድብሃል። ደራሲያን እንዲጠይቁህ፣ እጅግ ስመጥር ሰዎችም በክፉ እንዲናገርብህ ይጠቀምባቸዋል።

ጲላጦስ፤ ሔሮድስ፤ ሐናንያ፤ ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ። ይሁዳም በአጠገብህ ቆሞ በሰላሳ ብር ሊሸጥህ ይከጅላል። ይሄ ሁሉ የደረሰብህ ሰይጣን በዚህ ከስራህ ሊስብህና እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ሊያሰናክልህ መሆኑን ልትገነዝብ አትችልምን?
ሥራህን ሥራ፦ አላማህ እንደ ኮከብ የጸና ይሁን ተወው አለም እንደፈለገው ይነታረክ ይጨቃጨቅ፡፡ አንበሳው ሲያጋራ ፍንክች አትበል የሰይጣንን ውሻዎችን ለመውገር አትቁም፡፡ ጥንቸሎችን በማባረር ጊዜህን አታጥፋ

ሥራህን ሥራ፦ ዋሾች ይዋሹ፣ ጠበኞች ይጣሉ፣ ማህበሮችም ይወስኑ፣ ደራሲዎችም ይድረሱ፤ ሰይጣንም የፈለገውን ያድርግ። አንተ ግን ምንም ነገር እግዚአብሔር የሰጠህን ሥራ ከመፈፀም እንዳያግድህ ተጠንቀቅ።

ሥራህን ሥራ፦ ገንዘብ እንድታተርፍ አልተላክህም፣ እንድትበለጽግም አልታዘዝክም፣ ለክብርህ ተከላከል ብሎ አልተነገረህም፤ ሰይጣን አገልጋዮቹ የሚነዙትን የሐሰት ወሬ እንድታስተባብል አልተጠየቅህም እነኚህን ሁሉ ነገሮች ብታደርግ ሌላ ሥራ ልትሰራ አትችልም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለራስህ እንጂ ለጌታ አልሰራህም።

ሥራህን ሥራ፦ አላማህ እንደ አለት የፀና ይሁን፣ ጥቃት ይደርስብህ፣ ትበደል፣ ትሰደብ፣ ትታማ፤ ትቆስልና ትናቅ ይሆናል። አንተ ግን በፀና ውሳኔ የማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላይ ፀንተህየሰጠኽኝን ሥራ ፈፀምኩ ሃይማኖትንም ጠበቅሁ” ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን አላማና የተፈጠርክበትን ግብ ተከትል።

  --------------------------------------------------------------------------------
        (ምንም ብታደርጉ ሠዎች *በአራቱም አቅጣጫ* ከማውራት ስለማይመለሱ ዝም ብላቹ ሥራችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ!!!)
   ---------------------------------------------------------------------------------

No comments:

Post a Comment