Sunday, November 24, 2013

ስለ ጾም ጠቃሚ ምክር፦



1. ጾም ማለት ከእግዚአብሔር የታዘዘ እውነተኛ ሕግ ነው። ነገር ግን የሥራውን ፍሬ መጀመሪያ እንገልጻለን፤ ጾም ማለት መጀመሪያ ዓይናችን ክፉ ነገርን እንዳያይ፤ ጆሮአችን ክፉ ነገርን እንዳይሰማ፤ አንደበታችን ክፉ እንዳይናገር መከልከል ነው እንጂ እንዲያው ሥጋና ቅቤን ብቻ መተው አይደለም።

መቼም የሰው ባሕርይ በዚህ ዓለም ሲኖር ሁል ጊዜ በደስታና በተድላ ለመኖር ነው የሚጥረው፤ ይኸውም ለሰው ልጅ ሐሳብ ሁለት መንገድ አለው፤ አንዱ በሕግ የተፈቀደ፤ ሁለተኛው በሕግ ያልተፈቀደ ነው። በሕግ ያልተፈቀደ ማለት እግዚአብሔርንና ሰውን የሚበድልበት የዓመጽና የኃጢአት ጎዳና ነው።

 አባታችን አዳም ከሕግ የወጣ መንገድ ያልታዘዘውን ሥራ ሠርቶ በልቶ ከገነት ወጥቶ ወደ ግዞት እንደሄደ ያመለክተናል። በሕግ የታዘዘ መንገድ ማለት ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ሀብታምም ቢሆን ወይም ድሃ፤ ያንኑ የመጀመሪያ ዕድሉ የሰጠውን ሀብት በምስጋና ተቀብሎ ፈጣሪውን እያመሰገነ በጾምና በጸሎት፤ ወይም በሐዘንና በደስታም ቢሆን እግዚአብሔርንና ወንድሙን ባይበድልና ሳያስቀይም ‹‹ላብህን ከግንባርህ ጠርገህ እንጀራህን ብላ›› /ዘፍ3፡19/ እንደተባለው ሕግን ቢፈጽም፤ እስከ ዘለዓለም የሕይወቱ ምንጭ ሳይደፈን ይኖራል።

የጥፋት ልጆች ዛሬ ግን ሰዎች ጾምና ጸሎትን እግዚአብሔር የማይፈቅደው ሕግ ነው፤ እግዚአብሔር የሚወደውና የታዘዘው ሕግ ያገኙትን ሁሉ ሳይጸየፉ መብላትና በደስታ መኖር ነው፤ ብለው በሆቴል ሜዳ ያገኙትን እንደ ጨፌ ሣር የለመለመ መብልና መጠጥ እየተመገቡ እናያለን። ነገር ገን ይህ እግዚአብሔር የሚወደው ሕግ ይሆን? በእውነት እግዚአብሔር የሚወደው ሰው አጭር ጊዜ በሆነ ሕይወቱ በዚህ ዓለም ላይ ሲኖር ለእርሱ ሲል የተሰቀለለትንና የሞተለትን ፈጣሪው ሁል ጊዜ እያሰበ በጾምና በጸሎት በሐዘንና በትዕግሥተ ሆኖ ወደ ፈጣሪው ዓይነ ሕሊናውን ሰቅሎ፤ ዘለዓለማዊ የሆነውን ብርሃናዊ ሕይወት ተጎናጽፎ መኖር ነው። በዚህ ዓለም ተድላና ሕይወት ለእኛ ነውና የተፈጠረው ብለው ሲፈነጥዙ፤ ቢኖሩ፣ ‹‹ሞት ሲመጣ ጥሩ ቄስ፤ ጦር ሲመጣ ግዙ ፈረስ›› የተባለው ተረት በእነርሱ ላይ ይፈጸማል

 
እኛ ከኃጢአት ቁስል የምንድነበትና የምንፈሰውበት በጾምና በጸሎት መሆኑን አንዘንጋ፤ ያለ ጾምና ያለ ሐዘን ደስታ /ሮሜ 5፡3-4/፤ ያለ ሥራም መክበርና ባለጠጋ መሆን አይገኝም፤ ያለዚህ ግን ደስታና ክብረት ቢገኝም እንኳ፤ እውነተኛ ክብረት እውነተኛ ደስታ ሊባል አይገባውም የሌብነት ክብረት ነው እንጂ።
 
በአሁኑ ጊዜ የስህተት ትምህርት እያስተማሩ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያቆራርጥን የሚያጣላ ስሕተት የመላበት ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ተነሥተዋል፤ እነ መምህር ሆድ አምላኩ የሚያስተምሩት ቃል ይህን ነው፤ ‹‹ሰውን የሚያረክሰው የበላው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም›› /ማቴ 15፡11/ የተባለው ንባብ ዛሬ በሁሉ ዘንድ የተጠና ሆኖአል፡፡ ነገር ግን ይህን ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ ከአሥርቱ ቃላት ወይም ከስድስቱ ቃላት እንደ ሕግ አድርጎ አልተናገረውም። ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርትህ እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና ሕጋችንን ይተላለፋሉ ብለው በጠየቁት ጊዜ ለነዚያ መልስ ሲሰጥ ሳይታጠቡ ቢበሉ እነሱን ነው የሚጎዳ እንጂ ሰውየውን ወይም የነርሱ እድፍ ሌላኛውን ያገኘውን ሰው አያረክሰውም ሰውን የሚያረክሰው ክፉ ንግግር ነው ብሎ ያስተማረውን ስለጾም በማስመሰል ሁሉ ብሉ ብሎናል እያሉ ያስተምራሉ። /ፊልጵ 3፡19/
 
ወንድሜ ሆይ አባታችንን አዳምን አምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን ያሳሰረው ማን ነው? አትብላ የተባለውን በመብላቱ አይደለምን? አዳም በመብል ምክንያት ያመጣውን ጠላት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጾም ድል እንደነሣው አታውቅምን? እወቅ!
 
ሐተታ ሳይበዛ ባጭሩ፣ እንዲያው ነቢያት ካህናት ሁልጊዜ ጠላታቸውን ድል የሚያደርጉት በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪ የሚመለሱበት መሆኑን አትርሳ፤ /ኢዩ 2፡12-15፣ ኤፌ 6፡18፣ ኤርም 36፡7-8/ ሆድ አምላኩ ሆይ እባክህ ልብ አድርገህ አስተውል ለአራዊትና ለአንስስት እንኳን ምግባቸው ልዩነት አለው ለእንስሳ ገለባ፣ ለበሬ ሥጋ ቢያቀርቡለት አይበላም፡፡ ክርስቲያንም በጾም ወራትና በፍስክ ወራት ለይቶ መብላት እንደሚገባው አይዘንጋ ሁልጌዜ ለሆዴ ማለት አምላኬ አዛዤ እርሱ ነው ያሰኛልና። /ሮሜ 16፡18/
 
ከላይ ከነቢያት ቃል የመነጨው፤ /1ኛ ሳሙ 6፡5-6፣ 2ኛ ዜና 20፡3፣ ዕዝራ 8፡23፣ ነህምያ 9፡1፣ ኢሳ 58፡3-9/ በሐዋርያት ቃል የጸደቀው /ማቴ 9፡14-17፣ ሐዋ 13፡1-3፣ ሐዋ 27፡9፣ 2ኛ ቆሮ 11፡27/ ሲያያዝ የመጣውን የቅዱሳን አበውን እምነትና ትምህርት ጎዳና አድርገው በዚያው መጓዝ ነው እንጂ ወንጌል ባልሄደበት ጎዳና ገሥግሦ የነቢያትን ትንቢት ጥሶ ምሳሌ አፍርሶ የአእምሮን መዝጊያ ሰብሮ የሚያስተምረውን የሚናገረውን መምህር መስማት በገዛ ራሳችን ላይ የኃጢአት መርዝ መነስነስ ነው።

2. ጾም የሥራ መጀመርያ ናት፣
   የጽሙናን ክብራቸው ናት፣
   የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው ናት፣
   የንጽሕና መገለጫ ናት፣
   የጸሎት ምክንት ናት፣
   የዕንባ መገኛ ናት፣
   አርምሞን የምታሰተምር ናት። /ማር ይሰሐቅ/

* ኃይለኛ መድኃኒት መርዘኛ ፍጥረታትን ነቃቅሎ እንድሚወጣ፤ ከጾም ጋር የተባበረ ጸሎትም ክፉ ሐሳቦችን ነቅሎ ይጥላል። /ቅድስት ጠንቀሊጠቃ/

-------------------------------------------------------
 1. አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ፣ መርሐ ልቡና፣ መጋቢት 24/1943 ዓ.ም፣ አ.አ. ትንሣኤ ዘጉባኤ ማ/ቤት፣ ገጽ 35-39
                 2. * ብሂለ አበው 2005 @ማኅበረ ቀዱሳን


1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete