Saturday, November 30, 2013

ፕሮቴስታንቶች (ተሐድሶ) የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስን አይቀበሉ፦



ፕሮቴስታንቶች (ተሐድሶ) በሐዲስ ኪዳን ውስጥ በማስረጃነት ደረጃ የተጠቀሰ ጥቅስ የለም ይላሉ። ይህ አባባላቸው የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በደንብ ካለማንበባቸው የተነሣ እንጂ በብዙ ቦታዎች እንደተጠቀሱ ማስረጃዎችን ከብሉይ ኪዳንም ከሐዲስ ኪዳንም እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል!

ፕሮቴስታንቶች (ተሐድሶ)፦ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚፈልጓቸውን ብቻ በመውሰድ ሌሎችን ትተዋቸዋል። በመሆኑም እነርሱ በሚቀበሏቸው እና ቤተ-ክርስቲያናችን በምትቀበላቸው መጻሕፍት ቁጥር መካክል ልዩነት አለ።

1.        የፕሮቴስታንቲዝም መስራች ማርቲን ሉተር ለእርሱ ትምህርት የማይመቹ የመሰሉትን መጻሕፍት እያወጣ ይጥል ነበር። ለምሳሌ፦ የያዕቆብ መልእክት ስለ ምግባር አስፈላጊነት ሰለሚያስተምርና ይህም ማርቲን ሉተር ስለ ጸጋ እና እምነት በቻ ይሰብከው ከነበረው ትምህርቱ ጋር አልሄድ ስላለው መልእክቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አውጥቶት ነበር። እንዲያውም “Epistle of straw ገለባ መልእክት” ብሎ እስከ መጥራት ደርሶ ነበር።

2.      አንዳንድ ወገኖች ከ66ቱ መጻሕፍት ውጭ ያሉትን መጻሕፍት “አፖክሪፓ” ብለው ይጠሯቸዋል። ይህ ግን የተሳሳተ ስያሜ ነው። “አፖክሪፓ” በጥንት ዘመን ምሥጢራዊ ለሆኑት የጥንቆላ መጻሕፍት የሚሰጥ ስም ነውና። እኛ ግን፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍቱን፦ “ሁለተኛ የቀኖና መጻሕፍት - ዲዮካትሮኒካል” እንላቸዋለን።

3.      የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁለት ዓይነት የኖና ክፍሎች አሏቸው። እነርሱም፦ የመጀመርያ-ፕሮቶካኖኒካል፣ እና ሁለተኛ- ዲዮካትሮኒካል ይባላሉ።


       የመጀመርያ /ፕሮቶካኖኒካል/፦ እነዚህ በካህኑ በዕዝራ የተሰባሰቡና መጀመርያ በቀኖና የተመዘገቡ ናቸው። /1ኛ መቃ 2፥10/ ነህምያም የነገሥታትን መጻሕፍት የያዘ ቤተ-መጻሕፍት አቋቁሞ ነበር። እነዚህ መጻሕፍት በሦስት የተከፈሉ ሲሆኑ፥ ቶራሕነበኢም እና ከተቢም ተብለው ጠራሉ። ዕዝራ እና ነህምያ ሁለተኛዎቹን መጻሕፍት በተመለከተ ያነሱት ነገር የለም። ምክንያቱም በዚያ ዘመን አልተሰበሰቡምና። የተሰበሰቡት ከእነርሱ በኋላ በመሆኑ፤ “ዲዮካትሮኒካል - ሁለተኛ” ተበለዋል።

ቶራሕ፦ አምድቱ የሙሴ መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን፤ በእኛ ሊቃውንት፥ “አምስቱ በሔረ ኦሪት” ተበሎ ይጠራል።


ነበኢም፦ የነቢያት መጻሕፍት የተካተቱበት ክፍል ሲሆን፤ እነርሱም፦ “ቀደምት ነቢያት” እና “ደኃርት ነቢያት” ተብለው ለሁለት ይከፈላሉ። “ቀደምት ነቢያት” የሚሏቸው፦ ኢያሱ፣ ሳሙኤል፣ እና ነገሥት ናቸው። “ደኃርት ነቢያት” የሚሏቸው ደግሞ ኤርምስ፣ ሕዝቅኤል፣ ኢሳስ እና አስራ ሁለቱ ደቂቃን ነቢያትን ነው። በሐዋርያት ሥራ 13፥15 ያነበቧቸው እነዚህን መጻሕፍት ነው።

ከተቢም፦ የታሪክ መጻሕፍት ማለታቸው ነው። እነዚህም በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን ታላላቅ እና “ታናናሽ የታሪክ መጻሕፍት ይባላሉ። “ታላላቅ የታሪክ መጻሕፍት” ማለትም፦ መዝሙራት፣ ኢዮብ፣ ምሳሌ፤ “ታናናሽ የታሪክ መጻሕፍት” ማለትም፥ መክብብ፣ መኃልየ መኃልየ፣ ሰቆቃው ኤርምያስ ናቸው። ከእነዚህም ቀጥሎ መጽሐፈ ዳንኤል፣ ዕዝራ፣ ነህምያ እና ዜና መዋዕልና ካዕል ይከተላሉ። እነዚህ ሁሉ ተጠቃለው የሙሴ ሕግ፣ ነቢያት እና መዝሙራት እየተባሉ ይጠራሉ።

ሁለተኛ /ዲዮካትሮኒካል/፦

1.        የሂጶ ጉባኤ በ393 ዓ/ም ዲዮካትሮኒካል መጻሕፍትን እውነተኝነትና ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆኑን አረጋግጧል።

2.      በ397 ዓ/ም የተደረገው የካርታጎ /ቅርጣግና/ ጉባኤም ተመሳሳይ ውሳኔ ሰጥቷል።

3.      በሦስተኛው መ/ክ/ዘ የነበሩት እነ ቀሌምንጦስ ዘሮም፣ እነ ዲዮናድዮስ ዘእስክንድር እንዲሁም ሲፕሪያን፤ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

4.      በአራተኛው መ/ክ/ዘ አበው እነ ባስልዮስ፣ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ዮሐንስ አፍወቅር፤ እየጠቀሱ አስተምረውባቸዋል።

5.      እነዚህ መጻሕፍት የሐዋርያት ቀኖና በተሰኘው የሐዋርያት ድንጋጌ ውስጥ በዝርዝር ተገልጠዋል።

6.     ጥንታውያን የሆኑት አብያተ ክርሰቲያናት፥ ማለትም፦ የካቶሊክ፣ የግሪክ ኦርቶዶክስ፣ እንዲሁም ኦርየንታል አብያተ ክርሰቲያናት ሁሉ ይቀበሏቸዋል። የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ስትቀበላቸው የኖረች ሲሆን፤ በሲኖዶስ ደረጃ በ1988 ዓ/ም ውሳኔ ሰጥታለች።

7.      በበጥሊሞስ ሁለተኛ ዘመን በ282 ቅ.ል.ክ በእስክንድርያ ብሉይ ኪዳንን ወደ ግሪክ የተረጎሙት ሰባ ሊቃናት ዲዮካትሮኒካል መጻሕፍትን አብረው ተርጉመዋል። የሰባ ሊቃናት ትርጉም ሦስት ቅጅዎች የሆኑት፦ የሲና፣ የእስክንድርያ እና የቫቲካን ቅጅዎችን ብንመለከት እነዚህን መጻሕፍት አካትተው እናገኛለን።

8.      በዮሐ 10፥22 የምናገኘው የመቅደስ መታደስ በዓል በሌሎች የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ አናገኘውም፤ በመጽሐፈ መቃብያን ወንድሞቹ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የወሰኑት በየዓመቱ መከበር ያለበት፣ የመታደስ በዓል ከመጽሐፈ መቃብያን በቀር ሌሎች የብሉያት መጻሕፍት ላይ አልተጠቀሰም። ነገር ግን ዮሐንስ በወንጌሉ 10፥22 ላይ ይህንን በዓል ጠቅሶት መገኘቱና ሌሎች ማስረጃዎች የመጻሕፍቱን ቅድሰና ያረጋግጡልናል። የሚገኘውም በ1ኛ መቃ 4፥59 ላይ ነው።

9.     በሉቃ 14፥13 “ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ” የሚለው ከጦቢት 4፥7፣ 10፥17 የተገኘ ነው።

10.   በ1ኛ ተሰ 4፥3 “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና ከዝሙት እንድትርቁ” የሚለው ቃል ከጦቢት 4፥13 የተገኘ ነው።

11.     በ1ኛ ቆሮ 10፥9 “ከእነርሱም አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑት በእባቦቹም እንደ ጠፉ ጌታን አንፈታተን” የሚለው ቃል ከዮዲት 8፥24 የተገኘ ቃል ነው።

12.    በ1ኛ ቆሮ 15፥32 “ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ” የሚለው ከጥበብ 2፥6 የተገኘ ቃል ነው።

13.   በዮሐ 7፥7 “ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል።” የሚለው የጌታችን ትምህርት በጥበብ 2፥13 ይገኛል።

14.   በሉቃ 16፥9 “እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ” የሚለው ትምህርት በሲራክ 14፥13 ይገኛል።

15.   በ1ኛ ጴጥ 1፥24 “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል” የሚለው ቃል ከሲራክ 14፥18 የተገኘ ነው።

16.   በሮሜ 13፥1 ፤ 1ኛ ጴጥ 2፥13 የተገለጠው “ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” የሚለው ቃል ከሲራክ 17፥14 የተወሰደ ነው።

17.   በይሁዳ 14 የተጠቀሰው “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።” በማለት የሄኖክ ትንቢት ጠቅሶ ጽፏል። በመጽሐፈ ሄኖክ 1፥9 ላይ ይገኛል።

18.   ወንጌላዊው ማቴዎስም በምዕራፍ 27፥9 ላይ፤ የመጽሐፈ ተረፈ ኤርምያስን ጠቅሶ “በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው፥ ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፣ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት፤ የሚል ተፈጸመ።” በማለት ጽፏል። ማቴዎስ ነቢዩ ኤርምያስን ጠቅሶ የፃፈው በ66ቱ የትንቢተ ኤርምያስ መጽሐፍ ውስጥ የለም።  ነገር ግን መናፍቃን (ተሐድሶ) አንቀበልም ከሚሉት መጽሐፍ ከተረፈ ኤርምያስ 7፥5 ይገኛል።

19.   አዳምና ሔዋን፥ አቤል እና ቃየን ቃየልን ወለዱ። ቃየል አቤልን ገድሎ ሸሸ። ከዚያም ሚስቱን ዐወቀ፣ ፀነሰችም። ይህቺ የቃየል ሚስት ከየት መጣች? እንደ ኦሪት ዘፍጥረት ከሆነ፦ በምዕ 24 ላይ፥ በዓለም ላይ ያሉት ሰዎች አራት ብቻ ናቸው። (አዳም፣ ሔዋን፣ አቤል፤ ቃየል) ነበሩ። የዚህን መልስ የምናገኘው በኩፋሌ 5፥8-17 ነው።

20.  በዕለተ ሆሳህና፥ ዘንባባ ይዘው ጌታችንን የኢየሩሳሌም ሰዎች ሲያመሰግኑት ውለዋል። የዚህ ትውፊት፥ ታሪካዊ አመጣጥ የሚገኘው፤ በዮዲት 15፥12 እና በኩፋሌ 13፥21 ላይ ነው።

21.    በትንቢተ ኤርምያስ 39፥15 ስለ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ የተነገረው ትንቢ ፍጻሜውን የምናውቀው፤ በተረፈ ኤርምያስ ከምዕራፍ ስምንት ጀምሮ ያለውን ስናነብ ነው።

በተጨማሪም፥ ተከራካሪዎች ካስወጧቸው እና ከማይቀበሏቸው የብሉያት መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው የሐዲስ ኪዳን ጥቅሶች አሉ።

ለምሳሌ፦  ጦቢት 4፥7 ከማቴ 6፥19-20 ጋር
ጦቢት 4፥16 ከማቴ 7፥12 ጋር
ዮዲት 8፥12 ከማቴ 4፥7 ጋር ብናነፃፅራቸው ተመሳሳይነታቸው በቂ ማሳረጃ ነው።

በመሠረቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ለማድረግ የግድ በሐዲስ ኪዳን መጠቀስ አለባቸው የሚል የሃይማኖት ድንጋጌ የለም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ፤ ለምሳሌ፦ ከመጽሐፈ አስቴር፣ ከመጽሐፈ መክብብ፣ ከመኃልየ መኃልየ ዘሰለሞን፤ በሐዲስ ኪዳን የተጠቀሰ የለምና ተቀባይነት የሌላቸው መጻሕፍት ናቸው በተባለ ነበር።

ስለዚህ ከአጠቃላይ መናፍቃን (ተሐድሶ) መጻሕፍትን በጥንቃቄ ካለማንበብ የተነሣ በሐዲስ ኪዳን አልተጠቀሱም ለሚሉት እነዚያ ካልተቀበሏቸው መጻሕፍት በሐዲስ ኪዳን እንደተጠቀሱ ተመልክተናል። እነዚህን  መጻሕፍት  የተቀበልናቸው በሐዲስ ኪዳን ስለተጠቀሱም ስላልተጠቀሱም አይደለም፤ ነገር ግን እውነተኝነታቸውን በማረጋገጥ ነው።


/ይቆየን/
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወድንግል ማርያም!


ምንጭ፦ “ኦርቶዶክስ መልስ አላት” መጽሐፍ፤ በዲ/ዳንኤል ክብረት 2000ዓ/ም ገፅ ከ51-56
   “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትምህርት” ለጥናት የተዘጋጀ ጹሑፍ፤ በመምህር ቸሬ አበበ

No comments:

Post a Comment